“በምድር ንጉሥ፣ በሰማይ ቅዱስ”

55

ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምድር መኳንንት የሚያጅቡት፣ መሳፍንት ለክብሩ የሚከቡት፣ የጦር አበጋዞች በዙሪያ ገባው የሚቆሙለት፣ አገልጋዮች የበዙለት፣ ሀገረ ገዢዎች፣ ባሕር የሚያቋርጡ ነጋዴዎች የሚገብሩለት፣ ለንግሥናው ክብር እጅ እየነሱ ሺህ ዓመት ንገሥ እያሉ የሚመኙለት ኀያል ንጉሥ።

በሰማይ መላዕክት ደስ የሚሰኙበት፣ ጻድቃን የሚወዱት፣ አምላክ በረከቱን ያሳደረበት፣ ጥበብን፣ ትዕግሥትን፣ አስተዋይነትን የሰጠው፣ ዘመኑ የተባረከ፣ ታሪኩም የተወደደ ይኾን ዘንድ የመረጠው፣ እርሱን ከሚወዱት ጻድቃን ጋር ያስቀመጠው፣ ያማረውን የብርሃን ልብስ ያጎናጸፈው ቅዱስ። ምድርን አስጊጧታል፤ ድንቅ ነገርን ሰጥቷታል፤ አለትን በቤተ መንግሥቱ ዙሪያ እንዳሉ አሸከሮች አዝዟል፤ በዓለም ታይቶ የማይታወቀውን ጥበብ ገልጧል፤ በመጽሐፍ የነበረውን በዓለት ላይ ቀርጿል፤ በሰማይ ያለውን በምድር አሳይቷል፡፡ የምትታየውን ምድራዊቷን ኢየሩሳሌምን፣ የምትናፈቀውን ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌምን ባማሩ የእጅ ጥበቦቹ አስጊጧቸዋል፤ የተቀደሱ አፍላጋትን፣ የተባረኩ መካናትን በአንድ ቋጥኝ ላይ አሳምሯል፡፡

እንደ ንጉሥ በዙፋን ላይ ተቀምጦ ይፈርዳል፤ ይሾማል፣ ይሽራል፤ ፍርድ ያስተካክላል፤ የጦር አበጋዞቹን እያዘዘ የሀገሩን ዳር ድንበር ያስከብራል፤ በኅብር በተሸለመ ፈረስ ላይ ተቀምጦ በየአውራጃዎቹ እየተመላለሰ የሀገሩን ሕዝብ ያበረታል፡፡ ሀገሩን ጠላት እንዳይደፍራት፣ ሠንደቋን እንዳይነካት ያደርጋል፡፡ እንደ ባሕታዊ ጮማ መቁረጡን፣ ጠጅ መጨለጡን፣ ባማረ አልጋ ላይ መተኛቱን፣ በዓለም አጫዋቾች እየተደሰቱ ዓለም ማየቱን ይተዋል፡፡ ይልቅስ በባዕት ገብቶ አብዝቶ ይጸልያል፤ ይጾማል፣ ለሀገሩ ፍቅር እና በረክት ይበዛ ዘንድ ስግደትን ያበዛል ንጉሥ እና ቅዱስ ላሊበላ፡፡

“ሞት እና የላሊበላ ሕንጻ ሁልጊዜ አዲስ ናቸው ” የተባለላቸውን በሠርክ ሲያዩያቸው፣ በሠርክ አዲስ ነገር የሚታይባቸው፣ በሠርክም እጹብ የሚባልላቸውን አብያተክርስቲያናትን የሠራው ላሊበላ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ገናና ታሪክ አለው፡፡ ላሊበላ መንግሥትን ከክህነት ጋር አጣምሮ መንፈሳዊውን አሥተዳደር ከሥጋዊው ጋር አስተባብሮ የኖረ ንጉሥ ነው። ንጉሥ ላሊበላ ከኢትዮጵያ ባሻገር በዓለም የማይረሳ እና ስሙን በድንጋይ ላይ ቀርጾ ያለፈ የታላቋ ሀገር የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነው። በዓለም ታላቅ ሥፍራ ከተሰጣቸው እና ምንጊዜም ሲወሱ ከሚኖሩት መካከልም ነው። የሃይማኖት ጋሻ የጥበብ መሐንዲስ ነው።

ጨለማው እየተባለ በሚጠራው አህጉር የሥልጣኔ ጮራ እንዲፈነድቅ አድርጓል። ለጥበብ፣ ለወንጌል፣ ለዕምነት፣ ለሀገር ክብር፣ ለወገን ፍቅር ታግሏል ይባልለታል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንደ ላሊበላ ንግሥናን ከቅድስና፣ ቤተ ክህነትን ከቤተ መንግሥት፣ መንፈሳዊ ሕይወትን ከስጋዊ ሕይወት ጋር አስተባብረው የኖሩ፣ አስተባብረው የመሩ ነገሥታት አሉ፡፡ ላሊበላ የታወቀ እና ዝናው የገነነ ገናና የኾነችውን የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ መሪ መኾኑንም ሥራው እና ዓለም በሙሉ ይመሰክርለታል።

አፈ መምህር አለባቸው ረታ ቅዱስ ላሊበላ እና አብያተ መቅደሱ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላሊበላ ከወንድሙ ከቅዱስ ገብረማርያም ሐርቤይ በእግዚአብሔር ፈቃድ የመንግሥቱን ሥልጣን ተቀብሎ ከነገሠ በኋላ የመጀመሪያ ተግባሩ የኢትዮጵያን ሕዝብ በበታቹ ኾነው የሚያሥተዳድሩ የተማሩ እና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ዘረኝነት እና ወገንተኝነት የማያጠቃቸው ሰውን የሚያከብሩ በገንዘብ የማይደለሉ ሐቀኞች እና እውነተኞች የኾኑ መርጦ ሕዝብ ያመነባቸውን ሾሟል። እንደ መሪ ወይም ንጉሡ የቀና እውነተኛ ከኾነ የበታቹም የማያዳላ ብሔራዊ እና ሃይማኖታዊ ሐቀኛ ፍትሕ የሚሰጥ ይኾናል ብለው ጽፈዋል።

ከጽንሰት እስከ ህልፈት ድረስ መንፈስ ቅዱስ እንዳልተለየው የሚነገርለት ላሊበላ በታሪክ ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወቱ ጎላ ብሎ ተጽፏል፡፡ እርሱ በዘመኑ የተስተካከለ አሥተዳደር፣ ፍትሕ የበዛበት፣ ፍርድ በመስጠት ኢትዮጵያን ከጎረቤቶቿ እና ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጋር በመልካም ዲፕሎማሲ በማገናኘት ገናና ታሪክ እንደጻፈም ይነገርለታል፡፡ ስክነት፣ ብልሃት፣ አርቆ አሳቢነት የእርሱ የመሪነት ጥበብ እንደኾኑም ይነገራል፡፡ ከበደ ሚካኤል የዓለም ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላሊበላ ብዙ ሥራ በመሥራቱ መልካም ስም ያገኘ ነው።

ላሊበላ ከልጅነቱ ጀምሮ በጣም ብልህ ነበር ይባላል። ይህ ንጉሥ በሃይማኖት በኩል የፈጸማቸው ሥራዎች ብዙ ስለኾኑ እና እሱም ራሱ ሕይወቱን ያሳለፈው በመንፈሳዊነት ስለኾነ ቅዱስ ኾኖ በሰኔ 12 ቀን ክብረ በዓል ይከበርለታል ብለው ከትበዋል። አንድርዜይ ባርትኒስኪ እና ዮአና ማንቴል ኒችኮ በጻፉት እና ዓለማየሁ አበበ በተረጎሙት የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን በተሰኘው መጽሐፍ ንጉሡ በስሙ በሚጠራው በላሊበላ ከተማ እስከ ዛሬ ድረስ ዝናቸው ያልደበዘዘውን፣ ከአለት ተፈልፍለው የታነጹ አብያተክርስቲያናት ታላቅ የታሪክ ባለውለታ አድርገውታል።

ሌሎች የዛጉዌ መሪዎችም አብያተ ክርስቲያንን እና ዓለማዊ ሕንጻዎችን አሠርተዋል። ነገር ግን የላሊበላ አብያተክርስቲያናት ብቻ ናቸው ከእነ ግርማ ሞገሳቸው ቁመው የሚገኙት። በኅብረ ቃል ቀመር ብንገልጸው በትክክል በዓለም ካሉት እጹብ ድንቅ ነገሮች አንዱ ነው ተብሎ ተጽፏል። ላሊበላ በዘመኑ የሠራቸው ታሪኮች ትውልድ የሚኮራባቸው፣ የዓለም ሰዎች ሊያዩዋቸው የሚጓጉላቸው ናቸው፡፡

ፍስሐ ያዜ የኢትዮጵያ የ5ሺህ ታሪክ ከኖህ እስከ ኢህአዴግ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላሊበላ መንግሥቱን ከወንድሙ ተቀብሎ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ተብሎ ሲነግሥ ስመ መንግሥቱ ገብረ መስቀል ተባለ። ላሊበላ ገናና እንዲባል ያስቻለውን ሥራ ሠራ። ይህም በዘመኑ የሠራቸው አስደናቂ ውቅር አብያተክርስቲያናት ናቸው። ላሊበላ ከአንድ ቋጥኝ ያሠራቸው ኪነ ሕንጻዎች በዘመኑ የነበሩትን ብቻ ሳይኾን እኛን እና የወደፊቱንም ትውልድ ሊያኮራ የሚችል ታላቅ ሥራ ነው። በዘመኑ የተሠራው የሥራ ውጤትም ከዓለም አስደናቂ ቅርሶች አንዱ ነው ብለው ጽፈዋል፡፡

ፍስሐ ቢል ግርሃም የተባለ አሜሪካዊ ተጓዥ እና ጸሐፊን ጠቅሰው ሲጽፉ ” እናንተ ኢትዮጵያውያን የኢየሩሳሌም ሰማያዊት ባለሀገሮች ናችሁ። በእኔ ዕምነት ገነት ማለት ይህች ሀገራችሁ ናት። ብዙ ሀገሮችን በጉብኝት አይቻለሁ። የግብጽ ፒራሚዶችን፣ የባቲካን ቤተ አምልኮዎችን፣ የግሪክ ቤተ ጣኦቶችን፣ ምድረ እስራኤልን እና ሌሎችንም ነገር ግን እንደ ላሊበላ ሕንጻዎች ያስደነቀኝ የለም።

ዛሬ ዓለም በጥበብ ይምጠቅ፣ ጨረቃን ይጎብኝ፣ ሕዋውን ይፈትሽ እንጂ የእናንተን አባቶች ሰማያዊ ጥበብ ሊደርስበት አልቻለም፤ በዚህ ልትመኩ ይገባችኋል” ብለዋል። ታዲያ የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን በአባቶቻቸው ታሪክ ከመኩራት ተሻግረው ታሪካቸውን ይጠብቁ? አዲስ ታሪክሰ ይሠሩ ይኾን?
ተክለጻድቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ኑብያ አክሱም ዛጉዬ እስከ አጼ ይኩኑ አምላክ ዘመነ መንግሥት በሚለው መጽሐፋቸው ሙሴ ኮንቲ ሮሲኒን ጠቅሰው ሲጽፉ በሀገሩ ንጉሡ በጣም ኀያል ገናና ነው፡፡ የግዛቱን ዙሪያ ከበዓል ቀን በቀር ዙሪያውን በእግር ለመድረስ የአንድ ዓመት ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ዘውድ ደፍቶ የነገሠው በቅዱስ ገብርኤል እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ነው ብለውም ጽፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ንጉሥ ወ ቅዱስ እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ላሊበላ ንጉሥ ሲኾን በሎሌ የተመሰለ ነው። የቤተሰብ ጌታ ሲኾንም በቤተሰብ የተመሰለ ነው። የመኳንንት ጌታ ሲኾን በተገዥ የተመሰለ ነው። የጾምን ፍሬ ከትዕግሥት ፍሬ ጋር የትሩፋቱን ፍሬ አሳየ። የትሕትናንም ፍሬ ከመዋረድ ፍሬ ጋር፣ የጸሎትንም ፍሬ ከቅንነት ፍሬ ጋር፣ የስግደትን ፍሬ ያለ ሰይፍ እና ያለ መረገጫ ከሰውነት የምትፈስ የሰማዕት ደም የምትመስል ላበትን ከማንጠፍጠፍ ጋር፣ የንጽሕናንም ፍሬ ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን ከመገስገስ ፍሬ ጋር፣ እንግዳ የመቀበል ፍሬንም ከምጽዋት ጋር፣ የፍቅርንም ፍሬ ከርህራሄ ፍሬ ጋር፣ የማክበር ፍሬንም ፈጽሞ ከማመስገን ፍሬ ጋር፣ የዝምታ ፍሬንም ካለመልመድ ፍሬ ጋር፣ ደሃ አደግን የመጠበቅ ፍሬም ቅዱስ ላሊበላ ከቀደሙ ቅዱሳን የበጎ ምግባራቸው ፍሬ ሠብሥቦ የያዘ ነው ይላል ገድለ ላሊበላ።

ንጉሥ ወ ቅዱስ ላሊበላ ከነጻ አልጎሰቆለም። ከተቀደሰም አልረከሰም። ከቀና አልጠመመም። ደግ ከኾነ አልከፋም። ለበጎ ሥራ ከጨከነ ወደ ኋላ አልተመለሰም ተብሎ ተጽፏል። እርሱ በተነሳ ቁጥር የሚነሱት በስሙ በምትጠራው ከተማ ያሳነጻቸው አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ የአብያተ ክርስቲያናቱ ኪነ ሕንጻ ጥበብ እስካሁን ማስደነቃቸውን ቀጥለዋል፡፡ የላሊበላ ገድል ሥነ አብያተክርስቲያናቱን ሲገልጽ የእነዚህን አብያተክርስቲያናት ሥራ መናገር በምን አንደበት እንችላለን? የውስጣቸውንስ እንተው እና የቅጽራቸውን ሥራ እንኳ መናገር አንችልም። ያየም በማየት አይጠግብም።

ልቡ አርፎ ከማድነቅ ችላ አይልም። ታሪኩን ይቆጥር ዘንድ ለሰው የማይቻለው በላሊበላ ድንቅ የኾነ ታሪክ ተሠርቷልና። በላሊበላም እጅ የተሠሩትን የአብያተክርስቲያናት ሕንጻ ሥራ ያይ ዘንድ የሚወደስ ሰው ቢኖር ይምጣ ባይኖቹም ይይ። የአሠራራቸውም ሁኔታ ብዙ ስለኾነ ሥራቸውን ሁሉ በየመልኩ በየዓይነቱ ዘርዝረን ልንናገር አንችልም። እርሱ የሠራቸው ኪነ ሕንጻዎች ሕያው ቅርሶች ናቸው። ገንዘብ የማይገዛቸው፣ ዋጋ የማይተመንላቸው፣ ወርቅ የማይለካቸው፣ አልማዝ የማይለውጣቸው ናቸው ይላል፡፡

ታላቁ ንጉሥ ላሊበላ ታላቅ ሥራን ሠርቶ መንፈሳዊ እና ዓላማዊ ተጋድሎውን ሲፈጽም ያረፈው በሰኔ ወር ነበር፡፡ ዲያቆን ፈንታ ታደሰ የአራቱ ቅዱሳን ነገሥታት እና የአካባቢው ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላሊበላ በተወለደ በ97 ዓመቱ ከአምስት ወር ሰኔ 12 ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

እረፍቱም በቤተ ማርያም በምዕራብ በኩል ከሚገኘው የደወል ቦታ በጸሎት ላይ እያለ አረፈ። በጊዜ እረፍቱም አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ተገኝተው ሥርዓተ ግንዘቱን ከፈጸሙ በኋላ ራሱ ባዘጋጀው ከክርስቶስ የግንዘቱ ምሳሌ ሥር በኾነው ቤተ ጎልጎታ ውስጥ ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል ብለው ጽፈዋል።
አፈ መምህር አለባቸው ረታ ቅዱስ ላሊበላ እና አብያተ መቅደሱ በተሰኘው መጽሐፋቸው ቅዱስ ላሊበላ በተወለደ በ97 ዓመት ከአምስት ወር 11 ቀን በነገሠ በ40 ዓመቱ አብያተ መቅደሶቹን በሃያ ሦስት ዓመት ፈጽሞ በ1197 ዓ.ም ሰኔ 12 ቀን በሞት ተለየ።

በዚህ ዓለም ኖሮ በሞት ስለተለየ ቅዱስ ሥጋው በቅዱሳን በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ በአባ ጉባ ባሕታዊ ስመ ሞክሼ ዳግማዊ ጉባ በተባሉት ተገንዞ በደከመበት በጸለየበት እና እኒህን ታሪካውያን አብያተ መቅደስ ባነጸበት ብዙ ትሩፋት በሠራበት በቤተ ጎልጎታ የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ተፈጸመ ብለው መዝግበዋል።

የቅዱስ ላሊበላ እረፍት በጥንታዊቷ ላሊበላ ከተማ በሃይማኖታዊ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ቅዱስ እና ንጉሥ ነውና ይወደሳል፡፡ ይሞገሳል፡፡ የቅዱሱ እና የንጉሡ የእረፍት ቀን ዛሬ ናት፡፡ ታላቅ ታሪክን ስለሠራህ፣ ትውልድን የሚያኮራ፣ የሀገርንም ስም ለዘመናት በታላቅነት የሚያስጠራ ታላቅ ሥራ ሠርተሃልና ክብር ይገባሃል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ በብሪክሱ ዓለም አቀፍ መድረክ የላቀ የዲፕሎማሲ ድል አስመዝግባለች” አቶ አዲሱ አረጋ
Next articleየክልሉን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በጋራ መሥራት እንደሚገባ ተጠቆመ።