“ኢትዮጵያ በብሪክሱ ዓለም አቀፍ መድረክ የላቀ የዲፕሎማሲ ድል አስመዝግባለች” አቶ አዲሱ አረጋ

35

ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሩሲያ ቪላዲቮስቶክ የተካሄደው የብሪክስ አባል ሀገራት ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም በስኬት ተጠናቅቋል፡፡ የጉባኤው ተሳታፊዎችም በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ 24 ነጥቦችን የያዘ የአቋም መግለጫ በማውጣት ለስኬታማነቱ እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

በመድረኩም ኢትዮጵያ የላቀ የዲፕሎማሲ ድል ማስመዝገቧን የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኅላፊ አዲሱ አረጋ ገልፀዋል። “ዓለማቀፋዊ ብዝኀነት፣ ለብዝኀ ዋልታ ሥርዓት” በሚል መሪ መልእክት ከሰኔ 9 እስከ ሰኔ 12 በተካሄደው ፎረም ጥቂቶች ብቻ የሚወስኑባት ዓለም፣ በብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት ስር ለሚገኘው አብዝሃኛው የዓለም ሕዝብ የፖለቲካ ተሳትፎ፣ የሃብት ተካፋይነት፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ፍትሃዊ መኾን እንዳለበት በአጽንኦት ተመክሮበታል ብለዋል። ኢትዮጵያም በብልጽግና ፓርቲ በኩል ጠንካራ የአብሮነት አቋሟን አሳውቃለች ነው ያሉት አቶ አዲሱ።

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፋዊ የአብሮነት ተግባር ከሊግ ኦፍ ኔሽን እስከ አሁኑ የተባበሩት መንግስታት በግንባር ቀደም የተሳትፎ ሚና እንደምትታወቅ ጠቁመዋል። ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት እስከ አፍሪካ ኅብረት እድገት ደረጃም የላቀ አስተዋጽኦ እንዳላት በወርቃማ የታሪክ መዝገብ መጻፉን አቶ አዲሱ አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት ለተወከሉበት ለብዙኅኑ የዓለም ሕዝብ ሁለንተናዊ ጥቅም መከበር በሚደረገው የጋራ ትግል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ.ር) እና በብልጽግና ፓርቲ የተጀመረውን ውጤታማ ተግባር እንዳሳየች አቶ አዲሱ ገልጸዋል። ከጉባኤው ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር በመምከር ተጨማሪ የዲፕሎማሲ ድል በማስመዝገብ ተባብሮ የመሥራት ዓለም አቀፋዊ አጋርነቷን ማስመስከር ችላለች ብለዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ ባወጡት የአቋም መግለጫ ጉዳዮች መካከልም በአፍሪካ ጉዳይ ከአፍሪካ ውጭ ያሉ ሀገራት በፖለቲካ፣ በወታደራዊ፣ በፖለቲካ እና በሰብዓዊ እርዳታ ላይ የሚያደርሱት ተጽእኖ ሊቆም እንደሚገባ ትኩረታቸው መኾኑን ገልጸዋል። ለዚህም በብሪክስ እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር የማጠናከሩን አስፈላጊነትም አጽንኦት ሰጥተዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ይሄንን ለማሳካት ከብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሕዝብ ተቋማት፣ ባለስልጣናት እና ባለሙያዎች የሚሳተፉባፉባቸው የባለ ብዙ ዘርፍ ተመሳሳይ የውይይት መድረኮችን አስፈላጊነት ማንሳታቸውም ተጠቅሷል። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በተሳተፈበት የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ፎረም በርካታ የቀጥታ እና የጎንዮሽ ውይይቶች ተካሂደውበታል::

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕዝብን በቅንነት ከማገልገል ጎን ለጎን የወረዳውን ሰላም ለማስቀጠል እንደሚሠሩ በሰሜን ጎጃም ዞን የደቡብ አቸፈር የመንግሥት ሠራተኞች ተናገሩ።
Next article“በምድር ንጉሥ፣ በሰማይ ቅዱስ”