
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ ”ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልእክት የውይይት መድረክ ተካሂዷል። በውይይቱ ከተሳተፉ የመንግሥት ሠራተኞች በተመደቡበት ሙያ ሕዝብን በቅንነት ከማገልገል ጎን ለጎን በወረዳው የታየውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ሁሉም አካባቢዎች እንዲሠፋ እና የጋራ ተጠቃሚነታችን እንዲረጋገጥ የዜግነት ግዴታችንን መወጣት ይኖርብናል ብለዋል።
የወረዳው ብልጽግና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ደሳለኝ አማረ በበኩላቸው የሕዝባችን ጥቅም ለማስከበር እና የአማራ ሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ በሚል ሽፋን ትጥቅ አንስተው ወደ ጫካ የገቡ ወገኖች በነፍጥ ሊመለስ የሚችል አንድም ጥያቄ ባለመኖሩ ከእውነታው ባለመራቅ የጋራ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጅታቸውን ሊያሳዩ ይገባል ብለዋል።
በአካባቢያችን የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ክልሉን ወደ ኋላ ከመመለስ እና ሌላ ተደራራቢ ችግሮችን ከማብዛት የዘለለ ትርጉም ባለመኖሩ በግጭቱ ከደረሰብን የኢኮኖሚ፣ ማኀበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ በመማር በአዲስ መንፈስ ለሰላም መስፈን በጋራ ልንረባረብ ይገባልም ብለዋል፡፡
በግጭት መካከል ኾነን የወረዳውን ልማት ለማስቀጠል የመንግሥት ሠራተኛው እያሳየው ያለውን ተነሳሽነት አጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ደግሞ የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ ስጦታው መርሻ ናቸው። አቶ ስጦታው ጨምረውም በቀጣይ የታጠቁ ኃይሎች ለሰላም እጃቸውን በመዘርጋት ለውይይት ዝግጁ እንዲኾኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!