“በጸጥታ ችግር ተቋርጠው የነበሩ የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ የተሥራው የዘመቻ ሥራ ውጤታማ ነበር” የምሥራቅ ጎጃም ዞን

9

ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ በጸጥታ እና በሌሎች ምክንያቶች በርካታ የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት አቋርጠው ነበር። የጤና አገልግሎቶችን እንደገና ተደራሽ ለማድረግ ለተከታታይ ሁለት ሳምንት የተሠራውን የዘመቻ ሥራ የሚመለከታቸው አጋር እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በደብረ ማርቆስ ከተማ እየገመገመ ነው።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ የሽዋስ አንዷለም እንደገለጹት በጸጥታው እና ሌሎች ችግሮች ምክንያት ክትባት አቋርጠው የነበሩ ሕጻናት ክትባታቸውን እንዲጨርሱ ማድረግ ተችሏል። መምሪያ ኀላፊው ተደራሽ ያልኾኑ ለኤች አይ ቪ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማፈላለግ የመመርመር ሥራ መሠራቱን እና በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት መድኃኒታቸውን ያቋረጡትንም ፈልጎ በማግኘት ወደ ህክምናቸው እንዲመለሱ ስለመደረጉ አስገንዝበዋል።

የቲቪ በሽታ ሊኖርባቸው ይችላል ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎችን መለየት እና ወደ ጤና ተቋም በመላክ ምርመራ እንዲያገኙ ማድረግ ስለመቻሉም ነው የገለጹት። የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ የጤና ተቋቋማት ባለሙያዎች እና መሪወች የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በራሳቸው በመፍታት ለኅብረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት ያደረጉት ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ዋና አሥተዳዳሪው በተለያዩ ሰበቦች አገልግሎቱን የሚያጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳይኖሩ ለማስቻል ከተቋሙ ውጭ ያሉ አጋር እና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል። በዞኑ ለአጭር ጊዜ በተካሄደው የሕጻናት ክትባት፣ ለኤችአይቪ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማፈላለግ የመመርመር ሥራ፣ የቲቪ ተጠርጣሪ ሰዎችን መለየት እና ወደ ጤና ተቋም በመላክ ምርመራ እንዲያገኙ ለማድረግ የተሠራው ሥራ አበረታች እንደኾነም አስረድተዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር ከእርግዝና ጀምሮ የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን በጋራ እና በርብርብ መፈጸም ይገባል ብለዋል። ጤና መምሪያው ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር ለሚያካሂደው የክትባት እና ሌሎች አገልግሎቶች ዘመቻ ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።

በምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ የዩኒሴፍ ቴክኒካል አማካሪ አበባው ስንሻው ዩኒሴፍ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሚገኙ 15 ወረዳዎች የሕጻናት ክትባት እና ሌሎች አገልግሎቶችን ለመስጠት የቤት ለቤት የመረጃ የመሠብሠብ ሥራ ለመሥራት በየወረዳዎች ውይይት ማካሄዱን ገልጸዋል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ፕሮጀክቱ 17 ሚሊዮን ብር አካባቢ በጀት መድቦ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ የቤት ለቤት መረጃ ለመሠብሠብ እና የክትባት አገልግሎት ለመስጠት የዘመቻ ሥራ እንደሚሠራም ነው ያብራሩት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሁመራ እና አካባቢው የተቋረጠውን ኃይል መልሶ ለማገናኘት የሚያስችል ሥራ ተጀምሯል።
Next articleሕዝብን በቅንነት ከማገልገል ጎን ለጎን የወረዳውን ሰላም ለማስቀጠል እንደሚሠሩ በሰሜን ጎጃም ዞን የደቡብ አቸፈር የመንግሥት ሠራተኞች ተናገሩ።