
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ከሰኔ 9/2016 ዓ.ም የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተቋርጧል። በሁመራ እና አካባቢው በተዘረጋው ባለ230 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ላይ በደረሰ ተፈጥሯዊ አደጋ ኃይል መቋረጡን የሰሜን ምዕራብ ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ዳይሬክተር ውበት አቤ እንዳስታወቁት የኃይል ተሸካሚ ምሰሶው የወደቀው በአማራ ክልሰ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከሁመራ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው እንድሪያስ ቀበሌ ነው። ሁመራ ከተማን ጨምሮ በዳንሻ፣ ባዕከር፣ ወፍ አርግፍ፣ ሶረቃ፣ ማይካድራ፣ አብደራፊ፣ አብርሃጅራ፣ አዲጎሹ እና አደባይ እንዲሁም በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች ከሰኔ 9/2016 ዓ.ም ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ተናግረዋል።
የወደቀውን የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ የቴክኒክ ቡድን ጥገና መጀመሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ ጥገናውን ለማጠናቀቅ እስከ 10 ቀናት ሊፈጅ እንደሚችልም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!