በመደራጀት እና በኅብረት ለሴቶች ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት መሥራት እንደሚገባ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አሳሰበ።

27

ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር የሴቶች የልማት ኅብረት መልሶ ማደራጀት እና የጥምረት ተቋማት የጋራ የምክክር መድረክ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። በምክክር መድረኩ በዞን እና ወረዳ የሚገኙ የሴት አደረጃጀት ተጠሪዎች እና ከጤና ተቋማት የተገኙ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

አሚኮ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች “የሴቶች የልማት ኅብረት” በሚል በአዲስ መልኩ የተጀመረው አደረጃጀት መነቃቃትን የሚፈጥር መኾኑን በማውሳት የውይይት መድረኩ በግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል። ከዚህ በፊት “የሴቶች የልማት ቡድን” የሚለው መጠሪያ አላስፈላጊ ሥም ተሰጥቶት መቆዬቱ አደረጃጀቱ አስፈላጊውን ሚና እንዳይወጣ እንቅፋት ኾኖ ቆይቶ ነበር ተብሏል።

ከስያሜ ጀምሮ ለውጥ በማድረግ “የሴቶች የልማት ኅብረት” በሚል አዲስ መጠሪያ ወደ ሥራ መገባቱ ከመድረኩ ተገልጿል። ሴቶች ከማኅበረሰቡ ግማሽ በላይ ቀጥር አላቸው። ውይይቱም ተሳትፏቸውን እና ተጠቃሚነታቸውን ለማሻሻል የሴቶች የልማት ኅብረት በሚኖረው ሚና ዙሪያ ያተኮረ ነው።

በተናጠል ተሠርተው ከሚመጡ ውጤቶች ይልቅ በመደራጀት እና በኅብረት በመሥራት ለሴቶች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት መሥራት እንደሚገባ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ተናግረዋል። የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን በቤተሰብ ደረጃ በተገቢው መልኩ ለመተግበር እና ለአጠቃላይ የልማት ሥራዎች የሴቶች ሚና ከፍተኛ ነው። በመኾኑም ከሴቶች አደረጃጀቶች ጋር በቅንጅት በመሥራት የልማት ሥራዎችን ማፋጠን እንደሚገባ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብደልከሪም መንግሥቱ ተናግረዋል።

ሴቶች ችግሮቻቸውን ለመፍታት አቅማቸውን አቀናጅተው በክልላቸው ልማት ላይ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሊኾኑ ይገባል ብለዋል። የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን በመተግበር ጤናን በቤተሰብ ደረጃ የማረጋገጥ ሂደት እንዲሳካ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል። በተለይም የእናቶችን እና ህጻናትን ሞት በመቀነስ ሂደት ውስጥ አደረጃጀቱ ሚናው የጎላ መኾኑ በምክክር መድረኩ ተነስቷል።

ዘጋቢ፦ ደምስ አረጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕዝቡ በፀጥታ ችግሩ ከፍተኛ ጫና እንደደረሰበትና ሕግ እና ሥርዓት እንዲከበርለት አጥብቆ እንደሚሻ ተገንዝበናል።” የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ከፋለ ሙላቴ
Next article“ሀገርን መውደዳችን በምንሰጠው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ልክ ይገለጻል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ