
ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መሪዎች እና የሕዝብ ወኪሎች በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሰላምን ለማምጣት ያለሙ ወይይቶችን አድርገዋል። በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት ካስከተለው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት በተጨማሪ በክልሉ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና ማሳደሩ በተደጋጋሚ ይነሳል።
በአማራ ክልል ምክር ቤት የአካባቢ ጥበቃ እና ውኃ ሃብት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከፋለ ሙላቴ ግጭቱ በክልሉ የግብርና እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል። ከዞኑ እና ከክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች ጋር በምሥራቅ ጎጃም ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ተዘዋውረው ከሕዝቡ ጋር የመከሩት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው በፀጥታ ችግሩ ሕዝቡ ከፍተኛ ጫና እንደደረሰበት እና ሕግና ሥርዓት እንዲከበርለት አጥብቆ እንደሚሻ መገንዘባቸውን ነግረውናል።
አቶ ከፋለ ምክር ቤቱ እስከታች ወርዶ ሕዝቡን ለማወያየት እና አስፈጻሚ አካላትን ለመቆጣጠር ግጭቱ ማነቆ ኾኖ እንደቆየበት ገልጸዋል። አሁን እየታየ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ አስፈጻሚውን ለመከታተል እና ሕዝቡን ለመደገፍ እየተንቀሳቀሱ መኾናቸውንም አስገንዝበዋል። አቶ ከፋለ የክልሉ ሕዝብ የአረንጓዴ አሻራ ልማትን እንዲያከናውን እና አርሶ አደሮች ደግሞ የመኸር የግብርና ሥራቸውን ተረጋግተው እንዲያከናውኑ ሁሉም ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!