“ታጣቂ ኃይሎች ለትጥቅ ያበቃቸውን አጀንዳ ወደ ሀገራዊ ምክክሩ ቢያቀርቡት ሁሉም አሸናፊ መኾን ይችላል” ኢዜማ

57

ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሥራ አሥፈጻሚ እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሴቶች ክንፍ ሠብሣቢ ቅድስት ግርማ እንደገለጹት ታጣቂ ኃይሎች ለትጥቅ ያበቃቸውን አጀንዳ ወደ ሀገራዊ ምክክሩ በማቅረብ ችግሮችን መፍታት ይገባቸዋል፡፡

ታጣቂዎች ከእርስ በእርስ ግጭት፣ ከመገዳደል እና ካለመግባባት ባለፈ መንግሥት እና ሥርዓት በድሎናል ብለው አጀንዳቸውን ወደ ሀገራዊ ምክክሩ በማምጣት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቢያሳውቁ ሁሉም አሸናፊ መኾን እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡ ጥያቄያቸውን በጠመንጃ ለማስመለስ የሚሞክሩ ኃይሎች በመዋጋት አትራፊ እና አሸናፊ መኾን ስለማይችሉ በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበትን አማራጭ ሊከተሉ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡

በሀገራዊ ምክክሩ አለመሳተፍ ቆመንለታል፣ እንታገልለታለን እና እንሞትለታለን የሚሉትን ሕዝብ አጀንዳ ወደፊት ወጥቶ እንዳይፈታ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ሥራ አሥፈጻሚዋ ችግሮችን በመነጋገር፣ በመወያየት እና በመመካከር በመፍታት ዘላቂ ሰላም ማስፈን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ እንደ ሥራ አሥፈጻሚዋ ገለጻ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በምክክሩ አንሳተፍም ማለታቸው ትክክል እንዳልኾነ ተናግረዋል፡፡

ፓርቲዎች በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት ቢሳተፉ ታግለው መቀየር የሚፈልጉትን የአሠራር ሥርዓት እና አጀንዳ ሰላማዊ በኾነ መንገድ ከመፍታት ባለፈ መንግሥትን ማስተማር ይችላሉ ነው ያሉት፡፡ የመንግሥት እና የፓርቲ አሠራር አንድ ላይ የተጣመረ በመኾኑ መንግሥትን እና ገዥ ፓርቲን ለመለየት ችግር የኾነበት የአሠራር ሥርዓት መኖሩን ገልጸዋል፡፡

ይህንን እና መሰል ችግሮችን ወደ ሀገራዊ ምክክሩ በአጀንዳ መልክ በማቅረብ እንዲፈታ ማድረግ ይገባል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ፓርቲዎች ከቀስቃሽ፣ ከሚያለያዩ እና ከሚያጋጩ አጀንዳዎች ራሳቸውን በማቀብ በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶችን ከመንግሥት እና ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡

ለረጅም ዓመታት የሀሰት ትርክት በመፍጠር አንድ የሚያደርጉ ነገሮችን በመተው እና የሚያለያዩ አጀንዳዎችን በማብዛት እርስ በእርስ የተገዳደልንባቸው ብዙ ችግሮች አሉ ያሉት ሥራ አሥፈጻሚዋ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ሁሉም ማኅበረሰብ ንግግርን፣ ምክክርን እና ውይይትን ባሕል ማድረግ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

እንደ ኢፕድ ዘገባ ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የእርስ በእርስ አለመግባባት፣ ግጭት እና ጦርነት የሚያወጣ በመኾኑ ማንም ሰው በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ባለማኩረፍ በንቃት በመሳተፍ የተረጋጋች እና ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ታማኝነታችን ለፈጣሪ፣ ለህሊናችን እና ለሕዝብ ነው” ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም
Next article“በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ የ2016 ዓ.ም ሀገር አቀፉ የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።