“ታማኝነታችን ለፈጣሪ፣ ለህሊናችን እና ለሕዝብ ነው” ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም

17

ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

በኢትዮጵያዊነት የዘመናት ኑባሬ መካከል በጋራ የተፈጠሩ አስደማሚ ድሎች የመኖራቸውን ያክል የተካማቹ ሀገራዊ ችግሮችም አሉ፡፡ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ድሎች በዓለም ሀገራት የፍትሕ አደባባይ ከፍ እንዳደረጓት ሁሉ የጋራ ችግሮቿ ደግሞ አንገት የሚያስደፉ እና በሀገራዊ አብሮነት ላይ ቅርቃር የኾኑ ስብራቶች ናቸው፡፡

እነዚህ ሀገራዊ ችግሮች ከሰፈር ወደ አደባባይ ወጥተው በምክክር እስካልታረቁ ድረስ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ሳንካ መፍጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ የሀገሪቷ ልሂቃን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከሚያነሷቸው የሀገረ መንግሥት ስብራት ፈውሶች መካከል ሀገራዊ ምክክር ይደረግ የሚለው ጥያቄ ሚዛን ይደፋል፡፡ ጥያቄውን ተከትሎም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመ ዓመታት አለፉ፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም እንደገለጹት ሀገራዊ ምክክሩ የመንግሥት ፕሮጀክት ሳይኾን የሀገር ፕሮጀክት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል ያሉት ኮሚሽነሩ አዲስ ተቋም ማደራጀት እና የአሠራር ሥርዓቶችን መዘርጋት ከሚጠይቀው ሰፊ ጊዜ እና አቅም አንጻር በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል ነው ያሉት፡፡

በዘመናት ሂደት መካከል የተቋሰልንባቸው ጉዳዮች አሉ ያሉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ችግሮቻችን በዘላቂነት ለማከም በመከባበር እና በመደማመጥ መንፈስ በሀገር አቀፍ ደረጃ መነጋገር አለብን ይላሉ፡፡ “ታማኝነታችን ለፈጣሪ፣ ለህሊናችን እና ለሕዝብ ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ እስካሁን ባለው ሁኔታ ማንኛቸውም አካል ተፅዕኖ አላደረጉብንም፤ ወደፊትም ያደርጉብናል ብለን አንጠብቅም ብለዋል፡፡ ለሕዝባችን ወሳኝ ሚና የሚጫወትን ተቋም ያለአግባብ ልናባክነው አንችልም ነው ያሉት፡፡

ቅሬታ ያለውን ማንኛውንም አካል ለማስተናገድም በራችን ምንግዜም ክፍት ነው ያሉት ኮሚሽነር መላኩ ኮሚሽኑ ማንንም የማግለል ተልዕኮም ኾነ ፍላጎትም የለውም ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ ባዘጋጀው የአሠራር ሥርዓት መሠረት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻችን ናቸው፤ ያላቸውን ሃሳብ ይዘው ወደ ምክክር መድረክ እንዲመጡ እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡ ለዘመናት የተጣባንን የጦርነት ባሕል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ቋጭተን ሀገራዊ የምክክር እና የውይይት ባሕልን መላበስ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየብሪክስ አባል ሀገራት የጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የጋራ ጉባዔ ትናንት በሩሲያ ሶቺ ከተማ ተጀምሯል።
Next article“ታጣቂ ኃይሎች ለትጥቅ ያበቃቸውን አጀንዳ ወደ ሀገራዊ ምክክሩ ቢያቀርቡት ሁሉም አሸናፊ መኾን ይችላል” ኢዜማ