
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ትናንት በተጀመረው ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ከጉባኤው ጎን ለጎን ከሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሊቀ መንበር ኢሪና ፖድኖሶቫ እና ከሌሎች የፍርድ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
ውይይታቸው ያተኮረውም የሁለትዮሽ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደነበር ከኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በውይይቱም ሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው እና ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ በሌሎች መስኮች ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚያስፈልግ ተነስቷል።
ከውይይቱ በተጨማሪ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነትም ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ ፍርድ ቤቶቹ በትምህርት፣ በስልጠና፣ በአይሲቲ፣ የቴክኖሎጂና አቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸው መኾኑም ተገልጿል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ከጉባዔው ጎን ለጎን ከሌሎች ሀገራት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በጉባኤው የነገ ውሎም የብሪክስ አባል ሀገራት ያወጧቸውን ሕጎች የማቀራረብ እና የማስማማት ሂደት በተመለከተ አቶ ቴዎድሮስ ገለጻ እንደሚያደርጉ ተነግሯል።
እስከ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም በሚቆየው ጉባዔ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል።
በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሩሲያ፣ የቻይና፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የሕንድ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የግብጽ፣ የኢራንና የቤላሩስ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች ተሳትፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!