ሰላምን ከማጽናት ባሻገር የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መኾናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

48

ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የእምነበረድ እና የቀርከሃ ፋብሪካዎችን ጎበኙ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት ጀምሮ በክልሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው እየጎበኙ ነው። ዛሬም በክልሉ የሚገኙ የእምነበረድ እና የቀርከሃ ፋብሪካዎችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን፣ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሐብታሙ ተገኝና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ሰላምን በማፅናት ያለውን የማዕድን እና የቀርከሃ እምቅ አቅም ለመጠቀም የተጀመረውን ሥራ አድንቀዋል።

በተለይም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ መኖሩን ተመልክተናል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ የግብርና ሥራዎች በተለይም የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር እና የአረንጓዴ አሻራ አፈጻጸምን ትናንትና ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የክልሉን እምቅ አቅም ለልማት የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት እና ምቹ የአየር ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት መሠረት የሚኾን ንቅናቄ መኖሩንም ጠቁመዋል።

የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው በክልሉ የወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ግራናይትን ጨምሮ ሰፊ የማዕድን ሃብት መኖሩን ጠቅሰው ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ እነዚህ አቅሞችን ወደ ልማት በማዋል ረገድ አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ በክልሉ ያለውን መጠነ ሰፊ የቀርከሃ ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋልም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየንግድ ሥርዓቱን ጤናማ እና የተሳለጠ ለማድርግ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡
Next articleየብሪክስ አባል ሀገራት የጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የጋራ ጉባዔ ትናንት በሩሲያ ሶቺ ከተማ ተጀምሯል።