
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች በሀገራዊ የዘርፎች አፈጻጸም እና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሄደዋል። በመድረኩ የማክሮ ኢኮኖሚው ሀገራዊ የዘርፎች አፈጻጸም እና የተገኙ ውጤቶች እንዲሁም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ11 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2017 በጀት ዓመት አቅጣጫዎች ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት መድረኩ ሁሉም አመራር እና ሠራተኛ በማክሮ ኢኮኖሚው ሀገራዊ የዘርፎች አፈጻጸም እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ተገቢውን ግንዛቤ ይዞ የድርሻውን መወጣት እንዲችል ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው፡፡
አፈጻጸሙ በአስተቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ኾነን መሥራት እና ውጤት ማምጣት እንደምንችል ያሳየ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ትጋት እና ብርታት መለያችን ኾኖ ከቀጠለ የታሰበውን ሀገራዊ ልማት እና ብልጽግናን እውን ማድረግ እንደምንችል የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ጥራት ያለው የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተደረገው ጥረትም ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል “ትኩረታችን ምርትን ብቻ ሳይሆን ምርታማነትን ማሳደግ እና የተሟላ ኢኮኖሚያዊ ነፃነትን ማግኘት ነው” ብለዋል። ለዚህም ሁሉም የበኩሉን ለመወጣት ርብርብ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!