
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሩሲያ ቭላዲቮስቶክ እየተካሄደ ያለው የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፎረም ዛሬ ሦስተኛ ቀኑን ይዟል። በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ የልዑካን ቡድን በፎረሙ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ብሪክስ ለዓለም ብዙኀን ማኅበረሰብ ፍላጎቶች የቆመ እና ለፍትሐዊ የዓለም የኢኮኖሚ እና ፋይናንሰ ሥርዓት የሚሠራ የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ የትብብር ማዕቀፍ መኾኑን ገልጸዋል። አቶ አደም ፋራህ የብሪክስ እና አጋር ሀገራት የፓርቲዎች ፎረም አካል የኾነ እና “የዓለም ብዙኀንን በሚወክሉ ሀገራት መካከል የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ትብብርን በማጎልበት ፍትሐዊ የዓለም ሥርዓትን እውን ማድረግ” በሚል ርዕስ በተካሄደ መድረክ ላይ ንግግር አድርገዋል።
ዓለም እርስ በእርሷ በተሳሰረችበት የአሁኑ ወቅት የኢኮኖሚ ትብብር ምርጫ ብቻ ሳይኾን ለሀገራት እጅጉን የሚያስፈልግ የግንኙነት ማጠናከሪያ መንገድ መኾኑን ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። ከኢኮኖሚ ኢ-ፍትሐዊነት አንስቶ እስከ አየር ንብረት ለውጥ እና የቴክኖሎጂ እድገት ልዩነቶች ድረስ እየገጠሙን ላሉ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች የጋራ ምላሽ መስጠት አለብን ብለዋል።
ብሪክስ የዓለም ነባር አሰራሮች እና ድንበሮችን ተሻግሮ የኢኮኖሚ ትብብርን ለመፍጠር እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ኢትዮጵያም የዓለምን አሁናዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ካስገባው የትብብር ማዕቀፍ ጋር ራሷን ይበልጥ ለማስተሳሰር እና የበኩሏን ድርሻ ለመወጣት ጽኑ ፍላጎት እንዳላት አመልክተዋል።
የብሪክስ አባል ሀገራት በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራትን ያገለለው እና ወደ ጎን የተወው ተለምዷዊ የዓለም የኢኮኖሚ ሥርዓት መቀጠል የለበትም በሚል ትግል እንዲደረግ እየተወጡት ያለው ሚና ቁልፍ መኾኑን ነው አቶ አደም የገለጹት። አባል ሀገራቱ የሃብት እና እድሎች ፍትሐዊ እና ተመጣጣኝ ስርጭት እንዲመጣ ይበልጥ መሞገት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ያለችው እና አምስተኛው የአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት ጋር ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነትን እየፈጠረች እንደምትገኝ ጠቅሰው ይህንኑ የትብብር አድማስ ለማስፋት እንደምትሻም አመልክተዋል። ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ትምህርት ከትብብር መስኮቹ መካከል የሚጠቀሱ መኾናቸውን ነው ያነሱት።
ትብብሮቹ ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለውን የልማት ጉዞ ማፋጠን ብቻ ሳይኾን በወዳጅነት እና በጋራ መከባበር ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር ማድረጉን ተናግረዋል። በፍትሐዊነት፣ በእኩልነት እና የጋራ ተጠቃሚነት ጽንሰ ሃሳቦች ላይ የቆመ ፍትሐዊ ዓለም መፍጠር እንደሚያስፈልግም አቶ አደም በአጽንኦት ተናግረዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት ለሌሎች አርዓያ የሚኾኑበት ልዩ እድል እጃቸው ላይ እንዳለ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!