
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕር ዳር ከተማ የ22 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክትን አስጀምሯል። በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ የአማራ ክልል እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባሕር ዳርን ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ራዕይ ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል። ለዚህም እውን መኾን የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ማስጀመር ውበት እና ምቾት እንዲኖራት ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ዛሬ የተጀመረው 22 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት፦
👉 ከደጃዝማች በላይ ዘለቀ አየር ማረፊያ – በጊዮርጊስ – ዓባይ ማዶ ገብርኤል
👉 ከመድኃኒዓለም – በፓፒረስ – አዲሱ የዓባይ ድልድይ – ዓባይ ማዶ የጎንደር መውጫ መንገድ
👉 ከአየር ማረፊያ – ማርዳ ቀለም ፋብሪካ – መብራት ኃይል፣
👉 ከአጂፕ – አዲሱ የዓባይ ድልድይ፣
👉 ከጊዮርጊስ – ፓፒረስ የሚያገናኝ መኾኑን ገልጸዋል። የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የሚገነቡ ሕንጻዎች ምንነት፣ ቅርጽ እና ቀለምም እንደሚወሰን ጠቅሰዋል።
ልማቱ በጥናት ላይ የተመሠረተ እውነተኛ እና የከተማዋን ታሪክ በጉልህ የሚያሳይ እንደኾነ ገልጸዋል። የከተማዋ የብስክሌት ታሪክም በመንገዶቹ እንደሚመለስ፤ ሌሎችም ምቹ የመጓጓዣ አማራጮች እና መገልገያዎችም እንደሚኖሩት ከንቲባው ጠቅሰዋል። ሕዝቡ፣ ባለሃብቶች እና የክልል ተቋማት ለልማቱ እንዲተባበሩም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጠይቀዋል። የክልል፣ የፌዴራል መንግሥትን እንዲሁም የከተማዋን ሕዝብ በማስተባበር የኮሪደር ልማቱ በውጤት እንደሚጠናቀቅ ነው የገለጹት።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በባሕር ዳር ከተማ የሚጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ በሌሎች የአማራ ክልል ሰባት ሪጅኦፖሊታን ከተሞችም እንደሚተገበር ገልጸዋል። የከተማ ልማቱ ከተሞች ራሳቸውን አልምተው እና አጽድተው ለነዋሪዎች ምቹ ለእንግዶች ሳቢ የሚኾኑበት መኾኑን ነው ርእሰ መሥተዳድሩ የገለጹት።
በአዲስ አበባ እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት ያለውን ጠቀሜታ እና ሳቢነት የጠቀሱት ርእሰ መሥተዳድሩ በሌሎች አካባቢዎችም መሰል ሥራ ለመሥራት ወኔ መፍጠሩን አስገንዝበዋል። የባሕር ዳርን የተፈጥሮ ውበት እሴት በመጨመር የበለጠ የምታምር እና የቱሪስት መስህብነት እንዲኖራት የተጀመረው የኮሪደር ልማት የበለጠ እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት።
የባሕር ዳርን ልማት የከተማዋ መሪዎች ብቻ ሳይኾኑ የክልሉ መሪዎችም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ነው ርእሰ መሥተዳድሩ ያብራሩት። በሌሎች ከተሞችም ተመሳሳይ ሥራ መሠራት አለበት ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ጎንደር እና ደብረ ማርቆስ ከተሞች የልማት ሥራውን መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ለከተሞች ልማት ድጋፍ እያደረጉ ነው፤ በዚህም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና የባሕር ዳር ተወላጅ ምሁራን አበርክቷቸው ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደርም ለባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ሙያዊ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው አመሥግነዋል። በቀጣይም ለኮሪደር ልማቱ ሁሉም የበኩሉን እንዲያበረክት ጥሪ አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!