
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 92 ተቋማት በኦዲት ግኝት መሠረት ተመላሽ እንዲያደርጉ አስተያየት ከተሰጠበት 443 ሚሊየን 23 ሺህ 846 ብር እና 23 ሺህ 55 ዶላር ውስጥ የተመለሰው 48 ሚሊየን 217 ሺህ 965 ብር ብቻ መኾኑ ተገለጸ፡፡ የፌደራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ በተቋማቸው የተከናወኑ ሥራዎችን ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡
በሪፖርቱም 92 መሥሪያ ቤቶች በኦዲት ግኝት መሠረት ተመላሽ እንዲያደርጉ ተብሎ አስተያየት ከተሰጠበት 443 ሚሊየን 23 ሺህ 846 ብር ከ91 ሣንቲም እና 23 ሺህ 55 ዶላር ውስጥ የተመለሰው 48 ሚሊየን 217 ሺህ 965 ብር ከ67 ሣንቲም ብቻ መኾኑ ተጠቅሷል፡፡
አፈጻፀሙም 11 በመቶ ብቻ ነው መባሉን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
በባለበጀት መስሪያ ቤቶች በኩል ርምጃ እስከመውሰድ የሚደርስ መሻሻሎች መኖራቸውን የጠቆሙት ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ነገር ግን ተቀባይነት የሚያሳጣ የኦዲት ግኝት እና ብር ተመላሽ ያላደረጉ መስሪያ ቤቶች ላይ ምክር ቤቱ ርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡ ምክር ቤቱ በበኩሉ በ2014 በጀት ዓመት በዋና ኦዲተር በኦዲት ግኝት መሠረት ብር ተመላሽ እንዲያደርጉ አስተያየት የተሰጠባቸው እና ተመላሽ ያላደረጉ ተቋማት ላይ ተጠያቂነትን እንዲሰፍን አሳስቧል፡፡
ተመላሽ መደረግ ከነበረበት ገንዘብ መካከል ተመላሽ የተደረገው 11 በመቶ ብቻ መኾኑ ተገቢ አለመኾኑን የገለጹት የምክር ቤቱ አባላት ችግሮቹን መመርመር በቀጣይም ገንዘቡን የማስመለስ እና ተጠያቂነትንም የማረጋገጥ ሥራ መከናወን አለበት ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!