የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ለ3 ሺህ አባዎራዎች የቤት መስሪያ ቦታ አስረከበ።

19

ደሴ: ሰኔ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ለ3ሺህ በማኅበር ለተደራጁ፣ ለአርሶ አደር እና ለአርሶ አደር ልጆች የቤት መሥሪያ ቦታ አስረክቧል። በልማት ተነሺ የኾኑ አርሶ አደሮች እና የአርሶ አደር ልጆች የቤት መስሪያ ቦታ ተረክበዋል። የቤት መስሪያ ቦታ የተቀበሉ አርሶ አደሮች እና የአርሶ አደር ልጆች ከተማ አሥተዳደሩ መብታቸውን አክብሮ መመሪያዎችን እና ደንቦችን ተከትሎ መሬት እንዲያገኙ በማድረጉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የቤት መስሪያ ቦታውን የተቀበሉ ማኅበራቶችም ይህ የመሬት ጥያቄ 10 ዓመት የፈጀ እና አራት ከንቲባዎች የተፈራረቁበት እንደነበር ተናግረዋል። አሁን ያለው አሥተዳደር ቁርጠኛ በመኾን የተለያዩ አስቸጋሪ አሠራሮችን በማለፍ የዓመታት ጥያቄያቸው መልስ እንዲያገኝ በማድረጉም አመሥግነዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ሥራ አሥኪያጅ ሲሳይ አየለ በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት በቀጣይ ለ300 ማኅበራት እና ከ15 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የቤት መስሪያ ቦታ ፈላጊዎች በከተማዋ በ4ቱም አቅጣጫ 4 ሳይቶችን በመለየት ቦታ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

የቤት መስሪያ ቦታ የመስጠቱ ዕቅድ የልማት ተነሺዎችን ያካተተ እንደኾነም ተገልጿል። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ ከተሞች ከሚፈተኑባቸው ፈተናዎች መካከል የመኖሪያ ቤት እጥረት አንዱ መኾኑን ጠቅሰዋል። ይህንን ችግርም ለመፍታት ከተማ አሥተዳደሩ ብዙ ችግሮችን አልፎ ዛሬ ላይ 3ሺህ ለሚኾኑ አባዎራዎች የቤት መሥሪያ ቦታ ማስረከቡን ገልጸዋል።

ቦታ ለተረከቡ ማኅበራት፣ አርሶ አደሮች እና ለአርሶ አደር ልጆች እስከዛሬ ላሳዩት ትዕግስት ምሥጋናቸውን ገልጸው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። እንደ መብራት እና ውኃ ያሉ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ ከተማ አሥተዳደሩ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡- መስዑድ ጀማል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleማኅበረሰቡ ከተረጅነት አስተሳሰብ ወጥቶ ወደ ምርት እንዲገባ ለማድረግ ፈፃሚ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡
Next articleበኦዲት ግኝት መመለስ ከነበረበት 443 ሚሊየን ብር በላይ የተመለሰው 11 በመቶ ብቻ ነው ተባለ።