
ደሴ: ሰኔ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ እና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በደሴ ከተማ ተካሂዷል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የደቡብ ወሎ ዞን እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል። በውይይት መድረኩ ላይ ማኅበረሰቡ ከተረጅነት አስተሳሰብ ወጥቶ ወደ ምርት እንዲገባ ለማድረግ ፈፃሚ አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
ከ560 ሺህ በላይ ዜጎች በልማታዊ ሴፍትኔት ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሊ ሰይድ የሚደረጉ ድጋፎች በቀጥታ ለተጎጂዎች እንዲደርሱ እየተሠራ ነው ብለዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ጋሎ አርሶ አደሩ ምርት እና ምርታማነቱን እንዲያረጋግጥ የሜካናይዜሽን ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ በማቅረብ፣ ከባሕላዊ አስተራረስ በማላቀቅ እንዲሁም በኩታ ገጠም አርሶ አደሩ እንዲያመርት በመደረጉ የተሻለ ውጤት እየመጣ እንደኾነ አቶ አህመድ ተናግረዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮነን በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋ ምክንያት በርካታ ዜጎች በዞኑ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸው እነዚህ ዜጎች በቋሚነት ወደነበሩበት ለመመለስ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ዞኑ ምቹ የኾነ እና ምርትን በከፍተኛ ሁኔታ ማምረት የሚችል መሬት መኖሩን ዋና አሥተዳዳሪው አብራርተዋል፡፡ አርሶ አደሩም ይህንን በመገንዘብ ከተረጅነት አስተሳሰብ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- ሰልሀዲን ሰይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!