
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሀ ግእዝ ብለው የቆጠሩት ቀዳሚ ታሪክ ጽፈዋል፣ ታላቅ ሀገር አውርሰዋል፣ ያልተበረዘ ማንነት፣ የራስ የኾነ እሴት፣ ትውፊት አኑረዋል፣ ሀ ግእዝ ብለው የቆጠሩት ሉዓላዊነትን አስጠብቀዋል፣ ነጻነትን አጽንተዋል፣ ሀገርን ከእነ ድንበሩ፣ ማንነትን ከእነ ክብሩ አቆይተዋል፣ በባዶ እግራቸው እየተመላለሱ ጥበብን ፈልገዋል፣ እንደ ውቅያኖስ ከጠለቀው ረቂቅ ጥበብ እየቀዱ ለዓለም ሁሉ አጠጥተዋል።
ከምድር እስከ ሰማይ የተዘረጋውን፣ በውኃ ውስጥ ያለውን፣ በሚታዩና በማይታዩ ዓለማት የተደበቀውን ምስጢር አስሰዋል፣ ከዋከብትን በየወገናቸው ለይተዋል፣ የጨረቃና የፀሐይን ምስጢር ፈልቅቀዋል። ዓለም በጨለማ ውስጥ በነበረበት ዘመን እንደ ከዋክብት አብርተው በጥበብ ተራቅቀዋል፣ እንደ ፀሐይ አብርተው ለዓለም ብርሃን ኾነዋል፣ እንደ ጨረቃ ደምቀው ጨለማውን ዓለም አድምቀዋል፣ ሀ ግእዝ ብለው የቆጠሩት የመላእክት ነገድ የዘመሩትን ዘምረዋል፣ ከመላእክት ጋርም ዘምረዋል፣ በሰማይ ያለን ዜማ ቀድተዋል፣ በሰማይ የታየውን በምድር አሳይተዋል፣ ፍጥረታትን በየወገናቸው፣ በየባሕሪያቸው አጥንተዋል።
ደበሎ ከለበሱት፣ ያለ ጫማ ከሚረማመዱት፣ በእንተ ስሟ ለማርያም ብለው ቁራሽ ከሚለምኑት፣ ለነፍስ ማድሪያ ከሚቀምሱት፣ የቅምጫና ውኃ ጠጥተው ከሚያድሩት፣ በደሳሳ ጎጆ ከሚኖሩት፣ አንገታቸውን ደፍተው ጥበብን በሚፈልጉት ደቀመዛሙርት ውስጥ ማንነቷ ያልተናወጸች፣ ባሕሏን የጠበቀች፣ ታሪኳን ያከበረች እውነተኛዋ ኢትዮጵያ አለች። በእነርሱ ልብ ያለችው ኢትዮጵያ በመከራ ጊዜ የምትረሳ፣ በተድላ ጊዜ የምትነሳ አይደለችም። ሁልጊዜም ከልብ በኾነ ፍቅር ትታሰባለች፣ እስከ ሞት ድረስ ትወደዳለች፣ በሞታው ትጸናለች። በተስፋ ትኖራለች፣ በአምላክ ትጠበቃለች፣ በመላእክት ክንፍ ትከለላች፣ በጻድቃን ጸሎት ትጠለላለች፣ በጠላቶቿ ፊት ገናና ኃያል ትኾናለች እንጂ።
በኢትዮጵያ ተራራዎች ከተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ተደጋግፈው የተሠሩ የሳር ጎጆዎች፣ ከድንጋይ በተሠራ መቀመጫ የተቀበጡ ደበሉ የለበሱ ልጆች ካያችሁ እነዚያ የእውቀት መሠረቶች ናቸው፣ እነዚያ ዓለም የሚታሰስባቸው፣ ሰማይና ምድር የሚታወቅባቸው፣ ሰውና ፈጣሪ የሚገናኙባቸው ቤቶች ናቸው። እነዚያ የጥበብ ዥረቶች ናቸው። እነዚያ የኢትዮጵያ ቀደምት ማንነት መቀረጫዎች ናቸው። እነዚያ የነጻነት እና የጥንታዊ ታሪክ መጎናጸፊያዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤቶች ሀገርና ሃይማኖትን ጠብቀው ኖረዋል። የቤተክርስቲያን አራት ዓይናዎች የሚወጡት፣ ዓለምን አጀብ ያሰኙ ሊቃውንት እንደ ምንጭ ውኃ የሚፈልቁት ከእነዚህ የአብነት ትምህርት ቤቶች ነው። የአብነት ትምህርት ቤቶች ለዓለም የተረፈ እውቀት ሰጥተዋል። እየሰጡም ነው፣ ይሰጣሉም። የኢትዮጵያ ቀደምትነት፣ ልዩነት፣ ነጻነት፣ ክብርና ማንነት የሚቀዳው ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች ነው።
ደበሎ ለብሰው ጀምረው፣ በባዶ እግራቸው ተንከራተው፣ ኮቸሮ ለምነው፣ በተባይ ተበልተው፣ እንቅልፍ አጥተው፣ ከመቃብር ቤት አድረው የእውቀት ቀንዲል ይኾናሉ። ዘመናትን እየዋጁ ለሰው ልጆች ያበራሉ። የነፍስ እና የስጋውን ሕይወት እና ተጋድሎ እያስማሙ ሰውን በስነ ምግባር ይቀርጻሉ። ከእነዚህ ጉባኤ ቤቶች የሚወጡ ሊቃውንት ታላቅ ሀገር አቆይተዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የደብረ ዓባይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር ዘላለም በሪሁን ጉባዔ ቤት በእግዚአብሔር መምህርት፣ በሙሴ ተማሪነት በደብረ ሲና እንደተጀመረ ይናገራሉ። ከሙሴ በኋላ የተነሱ ነብያትም ሲያስተምሩ ነበር፣ ክርስቶስ አዳምና ልጆቹን ለማዳን ወደ ምድር በመጣ ጊዜም ወንጌልን ያስተምር ነበር ነው የሚሉት።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሠረቷን ክርስቶስን አርዓያ አድርጋ ምሳሌ መስላ፣ ትርጓሜ ተርጉማ፣ ምስጢር አሜስጥራ ስታስመር ኖራለች፣ አሁንም እያስተማረች ምስጢር እያሜሰጠረች ናት። የጉባኤ ቤት ሰንሰለት ሳይቋረጥ ጉባዔ ቤቷን ዘርግታ፣ ደቀመዛሙርቱን ከመምህሩ እግር አስቀምጣ ታስተምራለች። ጉባኤ ቤቶች የእውቀት፣ የጥበብ የፍልስፍና፣ የምሕንድስና ማዕከላት ናቸው፣ ለሀገርና ለቤተክርስቲያን ያደረጉት አስተዋጽኦም የላቀ ነው ይላሉ መምህር ሐረገወይን።
ጉባኤ ቤቶች ለቤተክርስቲያን እስትንፋስ ናቸው፣ እስትንፋስ ብቻም አይደሉም፣ ቤተክርስቲያን ከጉባዔ ቤት ትወለዳለች ነው የሚሉት። ከዲያቆናት እስከ ፓትርያርኩ ድረስ ያሉት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እና ጠባቆች የሚገኙት ከጉባኤ ቤቶች ነው። ትናንት በባዶ እግራቸው እየተመላለሱ፣ ደበሎ እየለበሱ በጉባኤ ቤቶች ሲቀጽሉ የነበሩ ደቀመዛሙርት የዛሬ ሊቃውንት፣ የዛሬ ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው።
የኔታ ሐረገወይን እንደሚሉት የቤተክርስቲያን አስተምህሮ እንዳይበረዝ እንደ ዓይን ብሌን የሚጠብቁ፣ ሀሰተኛች ሲነሱ ጉባዔ ሠርተው፣ ኃይለ ቃል አውጥተው፣ ተከራክረው ረትተው ቤተክርስቲያንን ከፍ የሚያደርጉት፣ ዶግመዋ ሳይፈርስ፣ ቀኖነዋ ሳይጣስ ስርዓተ አምልኮዋ ሳይለወጥ ከእነ ሙሉ ማንነቷ ከዚህ የደረሰችው ከጉባኤ ቤት በወጡ ሊቃውንት ነው። የቤተክርስቲያን መሠረትም ጉልላትም ደቀመዛሙርት የሚሰባሰቡባቸው ጉባዔ ቤቶች ናቸው።
ጉባኤ ቤቶች ሙሉ ማንነት ያላት ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ማንነት ያላት ሀገር ያስረከቡ፣ ኢትዮጵያ አምልኮተ እግዚአብሔርን ጠብቃ እንድትኖር ያደረጉ፣ ቋንቋን ከእነ ፊደሉ፣ ስነ ጽሑፍን ከእነ አመሉ፣ ዜማን ከእነ ምልክቱ፣ አቡሻህር ከእነ ቀመሩ፣ ስነ ሕንፃ ከእነ ስዕሉ፣ የስነ ከዋክብት ጥበብን፣ የአስተዳደር ሕግን፣ ባሕልን ከእነ እሴቱ ያስረከቡ ናቸው ይላሉ። ጉባኤ ቤቶች ታላቅ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ታላቅ ሀገርም አስረክበውናል ነው የሚሉት የኔታ ሐረገወይን። ታዲያ ይሄን ውለታ የዋሉ ጉባኤ ቤቶች ዛሬ ላይ ጠባቂ አጥተዋል፣ ደጋፊም ተነፍገዋል።
ቤተክርስቲያንም፣ ኢትዮጵያም ወደፊት የሚያስፈልጓት ሊቃውንት የሚወጡት ከእነዚህ ቤቶች ነው፣ ሰበዓዊነት የሚቀረጸው፣ ሞራል የሚገነባው፣ ከመከራ የሚወጣው በእነዚህ ሊቃውንት ነው። ሰውን ሰው የሚያደርጉ፣ ምግባር የሚያውቅ፣ ሃይማኖትን የሚጠብቅ ትውልድ ይፈጠር ዘንድ ከጉባኤ ቤት የሚወጡ ሊቃውንት ያስፈልጋሉ።
እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሙሴ ያስተማረው ትምህርት ነው፣ ሕዝብ እንዴት መመራት እንዳለበት፣ ሃይማኖት እንዴት መጠበቅ እንዳለበት ነውና ጉባዔ ቤቶችም መጠበቅ አለባቸው። ጉባኤ አሁን ያሉት መምህሩ በሚያስተምሩት፣ ምዕምናን ሠርከ ሕብስት በሚሰጡት፣ ደቀመዛሙርቱም ጠንከረው በመማራቸው ናቸው ይላሉ። የኢትዮጵያ ታላቅነት የሚመነጩት ከዚህ ነው። የቀደመው ጥበብ እና እውቀት እንዲገለጥ ጉባዔ ቤቶችን መጠበቅ ይገባል ነው ያሉት። መንፈሳዊ ዲያቆናት፣ ቀሳውስት፣ መነኮሳት ፣ ሊቃነ ጳጳሳት ይኖሩ ዘንድ ጉባኤ ቤቶች መኖር አለባቸው። ጉባዔ ቤቶች ካሉ ሀገር እና ቤተክርስቲያን እስከነ ሙሉ ክብራቸው እስከ ምጻት ዘመን ድረስ ይቆያሉ ይላሉ መምህር ሐረገወይን።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!