ጣፋጩ የደቅ ማንጎ፡፡

18

ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ደቅ ደሴት በጣና ሐይቅ ላይ ካሉት ደሴቶች ሁሉ ትልቁ ደሴት ነው፡፡ ከባሕር ዳር ከተማ በ37 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የደቅ ደሴት ከባሕር ዳር በጀልባ 3 ሰዓት የሚፈጅ እና ከባሕር ዳር በስተሰሜን የሚገኝ ደሴት ነው፡፡ የደቅ ደሴት ከ10 ሺህ ያላነሰ የማኅበረሰብ ክፍል የሚኖርበት እንደኾነ ሲገመት ከደሴቱ አጠቃላይ ክፍል ሩብ የሚኾነው ለግብርና ሥራ ይውላል፡፡

የደቅ ማኅበረሰብ ዋነኛ መተዳደሪያው እርሻ ሲኾን በዋነኛነት ደግሞ የዳጉሳ፣ የበቆሎ እና የጤፍ ሰብሎች ይመረታሉ፡፡ ከፍራፍሬ ደግሞ ደቅ በማንጎ ምርቱ ይታወቃል፡፡ 1 ሺህ 333 የሚኾኑ የደቅ ደሴት አርሶ አደሮች በ69 ሄክታር መሬት ላይ በዓመት 185 ሺህ ኩንታል ማንጎ እንደሚያመርቱ ከዙሪያ ወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በጣፋጭነቱ በብዙ የፍራፍሬ ተጠቃሚዎች ዘንድ ተመራጭ የኾነው የደቅ ማንጎ አብዛኛው የምርቱ መዳረሻ ባሕር ዳር ከተማ ናት፡፡ ያም ኾኖ ግን የደቅ ማንጎ ከባሕር ዳርም ባለፈ በጎንደር፣ በደብረ ማርቆስ እና በአዲስ አበባ ገበያዎችም ለተጠቃሚዎች እየደረሰ መኾኑን ነጋዴዎች አረጋግጠውልናል፡፡

ቄስ አበበ ገሠሠ በደቅ ደሴት ላይ ማንጎ ከሚያመርቱ አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ የደቅ የማንጎ ተክል ለደሴቱ ልዩ ውበት ከመኾኑም ባሻገር እኛ አርሶ አደሮችን በገቢ ተጠቃሚ ያደረግን ነው ይላሉ፡፡ የደቅ ማንጎ ከአሶሳ፣ ከጋምቤላም ኾነ ከደቡብ ከሚመጣው ማንጎ በተሻለ ጣፋጭ ነው ያሉት ቄስ አበበ ችግሩ በማንጎ ምርቱ አርሶ አደሮች የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ አለመኾናቸው እንደኾነ ገልጸውልናል፡፡

የማንጎ ምርቱን ማራገፊያ ወደብ ማጣት፣ የመሸጫ ቦታ አለመኖር እና የጀልባ እጥረት የደቅ ማንጎ ፈተናዎች መኾናቸውንም ነው ቄስ አበበ የገለጹት፡፡ “እኛ አምራቾቹ በብዙ ልፋት የምናመርተውን ማንጎ በቀላሉ የሚጠቀሙበት ባለ ጀልባዎች፣ ባለ ጋሪዎች፣ ቸርቻሪዎች እና ሌሎችም ነጋዴዎች ናቸው” ያሉት ቄስ አበበ እነዚህ ችግሮች ቢቀረፉ የደቅ አርሶ አደሮች በእጅጉ ተጠቃሚ እንደሚኾኑም ገልጸውልናል፡፡

ሌላኛው በደቅ ደሴት ላይ ማንጎ አምራች የኾኑት አጉማሴ ውበት በበኩላቸው በዓመት ሁለት ጊዜ ለገበያ በሚደርሰው የደቅ ማንጎ እሳቸውን ጨምሮ ብዙ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መኾናቸውን ይናገራሉ፡፡ ምንም እንኳን በደቅ ደሴት ላይ እንደ በቆሎ፣ ዳጉሳ እና ጤፍ ሰብሎች ቢመረቱም ለእነዚህ ምርቶች የሚኾነው የአፈር ማዳበሪያ የሚገዛው ግን ከማንጎ ምርት በሚገኘው ገቢ መኾኑንም ጠቅሰውልናል፡፡

የደቅ ማንጎ የራሱ የኾነ መለያ ቢኖረው ምኞታቸው እንደኾነ የገለጹልን አቶ አጉማሴ ከዚያ በፊት ግን ለማንጎ አምራቾቹ የገበያ ትሥሥር መፈጠሩ፣ የማራገፊያ ወደብ፣ የማንጎ ማቆያ መጋዘን መኖር እና ሌሎች ሥራዎች መቅደም እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡ በሳምንት ሁለት ቀናት (ማክሰኞ እና አርብ) ብቻ ከደቅ ወደ ባሕር ዳር ማንጎውን በማምጣት ለተጠቃሚ ከማድረስ ባሻገር የማንጎ ምርቱ በዛፉ ላይ እያለ ሳይበላሽ በፊት ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ በማስቻል ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

“የደቅ ማንጎ በጣዕሙ ተወዳዳሪ እንደሌለው ለማረጋገጥ ማንጎውን መቅመሱ ብቻ በቂ ነው” ያሉት አቶ አጉማሴ ይሄንን የተፈጥሮ ጸጋ በአግባቡ በመጠቀም ደቅ ደሴትን እና የማንጎ አምራቾቿን ለማስተዋወቅ ሁሉም ርብርብ ያድርግ የሚል ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡ “ለአርሶ አደሮች ሥልጠናዎችን በመስጠት እና የሙያ ድጋፍ በማድረግ ጭምር የደቅ ደሴት የማንጎ ምርት እንዲጨምር ጥረቶች ተደርገዋል” ያሉን ደግሞ በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የመስኖ አግሮኖሚስት ባለሙያ አለነ የኔዋ ናቸው፡፡

የደቅ ማንጎን የማራገፊያ ወደብ፣ የመሸጫ ቦታ እና ሌሎች የአርሶ አደሮቹ ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸው ናቸው ያሉት ባለሙያው የአርሶ አደሮቹ ጥያቄ በተደጋጋሚ ጊዜ ለባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የቀረበለት ቢኾንም እስካሁን ከተስፋ የዘለለ አጥጋቢ ምላሽ አለመገኘቱንም ገልጸዋል፡፡ የደቅ ማንጎን በራሱ መለያ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ በማሰብ የዓለም የምግብ ድርጅት ባቀረበው የገንዘብ ድጋፍ የማንጎ መጭመቂያ እና ማስቀመጫ ማሽኖች መገዛታቸውን የገለጹት አቶ አለነ ማሽኖቹን ማስቀመጫ ቦታ ከመታጣቱ ጋር በተያያዘ ማሽኖቹ አገልግሎት ላይ አለመዋላቸውንም ገልጸውልናል፡፡

የደቅ ማንጎ አርሶ አደሮች በምርታቸው ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የደቅ ማንጎን በስፋት ለማስተዋወቅ፣ ምርቱን የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ለማድረግ እና ለሌሎችም ተግባራት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት የየራሳቸውን የቤት ሥራዎች መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው ባለሙያው ያሳሰቡት፡፡

በአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የገበያ መሠረተ ልማት አሥተዳደር እና ማስፋፋት ዳይሬክተር ግርማ ማርቆስ የደቅ ማንጎ አምራቾችን ጨምሮ ሌሎችም በባሕር ዳር ዙሪያ የሚገኙ አትክልት እና ፍራፍሬ አምራቾች በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በሚገኙ ሦስት የግብይት ቦታዎች ላይ ምርታቸውን መሸጥ ይችላሉ ብለዋል፡፡

አምራቾቹ ለባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጥያቄያቸውን በማቅረብ በሚያመቻቸው የገበያ ቦታ ላይ ምርታቸውን እንዲሸጡ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀሰተኛ የመረጃ ስርጭትን በበቂ ሁኔታ ለመታገል የወቅቱን የሚዲያን ባሕሪ መገንዘብ ወሳኝ ነው ” አቶ አዲሱ አረጋ
Next article“ሀ ግእዝ ብለው የቆጠሩ፤ ኢትዮጵያን ያኖሩ”