
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እየተስፋፋ ያለውን ሀሰተኛ መረጃ በበቂ ሁኔታ ለመታገል የወቅቱን የሚዲያ ባሕሪ በአግባቡ መረዳት አስፈላጊ እንደኾነ በብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኀላፊ አዲሱ አረጋ ገልጸዋል። በብልጽግና ፖርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ የልዑክ ቡድን ከሰኔ 9/2016 ዓ.ም እስከ ሰኔ 12/2016 ዓ.ም በሚካሔደው እና ዎርልድ ማጆሪቲ ፎር መልቲፖላር ኦርደር በሚል መሪ መልዕክት በሩሲያ ቪላዲቮስቶክ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ነው።
“ኀላፊነት የተሞላበት የመረጃ ስርጭት ፍትሐዊ የዓለም ሥርዓትን ከመገንባት አንጻር” በሚል ርዕስ በተስተናገደው የፎረሙ ክፍል ላይ አቶ አዲሱ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት ያልተረጋገጠ የተዛባና ሀሰተኛ መረጃ ኀላፊነት በጎደለው መልኩ በፍጥነት የሚሰራጭበት ሁኔታ እየታየ ነው ብለዋል። የዚህ ዓይነቱን ችግር ለመቋቋም ቴክኒካዊ መፍትሔ ብቻ ሳይኾን ዘመኑን ታሳቢ ያደረገ የሚዲያ ባህርያት የመረዳት ባሕል ሊዳብር እንደሚገባም አስረድተዋል።
በዚህም ለእውነት፣ ለትክክለኛነት፣ ለታማኝነት እና ለግልጽነት ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። አቶ አዲሱ እነዚህን የድህረ እውነት ዓለም ፈተናዎች ለመቋቋም ካቀረቧቸው ሃሳቦች መካከል ሕዝቡ የሚሰራጩ መረጃዎችን ትክክለኛነት እና የመረጃ ምንጩን ተቀባይነት እንዲያጣራ ማስተማር ቀዳሚ መኾኑን ተናግረዋል።
ሃሳብን በነጻነት የመግለጽን መብት ባከበረ መልኩም ሀሰተኛ የመረጃ ስርጭቶችን መከላከል የሚያስችል የተጠያቂነት የሕግ ማዕቀፎችን ተግባራዊ የማድረግን አስፈላጊነትም አንስተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በመንግሥት እና መረጃን በማጣራት በተሰማሩ አካላት መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ተከታትሎ ማጋለጥ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የዲጂታል ፖሊሲ የዜጎችን ብዝኃነት ታሳቢ ያደረገ ሁሉንም ማኅበረሰብ ያማከለ እና የወደፊቷን ዲጂታል ኢትዮጵያ ለመገንባት የሚያስችል መኾኑንም ገልጸዋል። የተሻሉ ተሞክሮዎችን እና ፈጠራዎችን በማጋራት፣ እድገትን፣ ደኅንነትን እና መረጋጋትን የሚያበረታታ ጠንካራ የዲጂታል አካባቢ መፍጠር እንደሚቻልም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከብሪክስ ጋር በጋራ በመሥራት የዲጂታላይዜሽንን የለውጥ አቅም ለመጠቀም ቁርጠኛ መኾኗን የገለጹት አቶ አዲሱ፤ በጋራ ፍትሐዊ ፣ አካታች እና ስኬታማ ዓለምን መገንባት እንደሚገባ ነው የተናገሩት። ኢዜአ እንደዘገበው በፎረሙ ላይ የብልጽግና ፖርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ በብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኀላፊ አዲሱ አረጋ፣ በብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር) እየተሳተፉ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!