ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎችን በመቅረፅ ሂደት ውስጥ ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች ምንድናቸው?

57

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር አጀንዳዎችን በማሰባሰብ እና በመቅረፅ ሂደት ውስጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ያከናውናል፡፡ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎችና ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ግልፅ፣ አካታችና አሳታፊ በሆነ መንገድ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ ምክር ቤት በየፈርጁ ተለይተው ከቀረቡ በኋላ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሆኑ አጀንዳዎች ይቀረፃሉ፡፡ በአጀንዳ ቀረፃ ሂደት ውስጥ ኮሚሽኑ የሚከተላቸው መርሆች ከዚህ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

1. ለምክክር ጉባኤው የሚቀርቡ አጀንዳዎችን መመጠን
ሀገራችን ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ እያለፈች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኮሚሽኑም በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ሲቋቋም በተለያዩ የፖለቲካ እና የሀሳብ መሪዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ልዩነት እና አለመግባባት መኖሩን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

በአንዳንድ መድረኮች እንደሚስተዋለው ኮሚሽኑ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ችግሮች መፍታት የሚችል ተደርጎ መወሰዱ ብሎም ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ የሚነሱ ጉዳዮችን እንደሚያስተናግድ መጠበቁ ሊስተካከል የሚገባው ዕይታ ነው፡፡ ኮሚሽኑ የተቋቋመው ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚረዱ ብሎም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር የመፍትሔ ሀሳቦች እንዲመነጩ ሁነኛ ሚናን ለመጫወት እንደሆነ ከወዲሁ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ኮሚሽኑ ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው የሚገቡ ሀገራዊ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ወደ ምክክር ጉባኤው እንዲቀርቡ የሚያደርገው፡፡

2. ድምፃቸው ጎልቶ የማይሰማ (minorities) የማህበረሰብ ክፍሎች አጀንዳዎች በአግባቡ መካተታቸውን ማረጋገጥ በተለያዩ ሀገራት በሚተገበሩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስርዓቶች ውስጥ ድምፃቸው ጎልቶ የማይሰማ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ኮሚሽኑ የተሰበሰቡትን አጀንዳዎች መሰረት አድርጎ ለሀገራዊ ምክክር የሚቀርቡትን ሲቀርፅ የእነዚህን ማህበረሰብ ክፍሎች ድምፅ ማንፀባረቅ መቻሉን የማረጋገጥ ሀላፊነት አለበት፡፡

3. ወቅታዊና እጅግ አንገብጋቢ ለሆኑ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ የሚሰበስባቸው ቀጥሎም የሚቀርፃቸው አጀንዳዎች በቁጥር ብዙ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢገመትም ሀገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ምክክር ሊደረግባቸው የሚገቡ እና አፋጣኝ መፍትሔን የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ያቀርባል፡፡

ኢትጵያ እየመከረች ነው!

Previous article“ሩዝን በ5 ዞኖች ለማልማት እየሠራን ነው” ግብርና ቢሮ
Next articleየባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።