
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከ20 እና 25 ዓመት በፊት የፎገራ፣ ሊቦ ከምከም እና የደራ ውኃ ገብ መሬቶች ጥቅም የማይሰጡ ከመኾናቸውም በላይ በአካባቢው የሚተኛው ውኃ ሰዎችን ለእንግልት እና ለእርዳታ ጠባቂነት ዳርጓቸው እንደነበር የአሁኑ ባለሃብት የቀድሞው እርዳታ ጠባቂ አርሶ አደር ጋሻው ጠና ይናገራሉ፡፡
አርሶ አደሩ እንደተናገሩት አካባቢው በውኃ ይጥለቀለቅ ስለነበር ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ከብቶቻቸውን ይዘው ክረምት በመጣ ቁጥር ወደ ተራራማ አካባቢዎች ሸሽተው ቆይተው ሲደርቅ ወደ ቀያቸው ይመለሱ ነበር፡፡ አርሶ አደሩ ያን ዘመን ሲያስታውሱ የዘሩት ሁሉ በውኃ ተጥለቅልቆ ባዶ እጃቸውን ስለሚቀሩ ለልመና እና ለእርዳታ ይዳረጉ ነበር፡፡
አርሶ አደሩ የነበረውን የከፋ ሕይወት ውኃ በላኝ ሲል ይገልጸው እንደነበርም ያስታውሳሉ። አሁንም ድረስ አካባቢው ሲከፋው እና ሲያዝን ውኃ በላኝ እንደሚል ነው የነገሩን፡፡ አሁን ላይ የነበረው ታሪክ ተቀይሮ ሌላ ሕይወት ውስጥ እንዳሉ የሚናገሩት አርሶ አደሩ በሩዝ ምርት ሕይወታቸው በመቀየሩ ታሪካቸውም ከውኃ በላኝ ወደ ውኃ አበላኝ መቀየሩን ነው የነገሩን፡፡ በሩዝ ምርት ወደ ባለሃብትነት መቀየራቸውንም ነው ያብራሩት፡፡
ልክ እንደ አርሶ አደር ጋሻው ጠና ሁሉ በርካታ አርሶ አደሮችም በሩዝ ልማቱ ሕይወታቸው ስለመቀየሩ ነው የሚናገሩት በዚህ ዓመትም በሩዝ ልማት ላይ ትኩረታቸውን በማድረግ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመጠቀም እንደሚያለሙ ነግረውናል፡፡ በግብዓት በኩልም አስፈላጊውን ሁሉ ለመጠቀም ዝግጁ እንደኾኑ ነው ያብራሩት፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው እንደገለጹት በዘንድሮው የምርት ዘመን የክልሉን የሩዝ ማሳ ሽፋን ወደ 188 ሺህ 631 ሄክታር መሬት ለማድረስ ታቅዷል። በሩዝ ምርት እንደ ክልል የተሻለ ልምድ አለ ያሉት ምክትል ኀላፊው በሀገር አቀፍ ደረጃ የሩዝ ምርትን ለማሳደግ የተጀመረውን ንቅናቄ በመጠቀም ምርቱን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
አቶ ቃልኪዳን በክልሉ ባለፈው የምርት ዘመን 82 ሺህ 279 ሔክታር መሬት በሩዝ ምርት መሸፈኑን አስታውሰው ዘንድሮ ወደ 188 ሺህ 631 ሄክታር ለማሳደግ እና በአንድ ሄክታር 53 ኩንታል የሩዝ ምርት ለማግኘት ታቅዷል። በክልሉ የሩዝ ምርት ውጤታማ በኾነባቸው አምስት ዞኖች በተለይም በደቡብ፣ ሰሜን፣ ማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች አዳዲስ አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የተሻለ ምርት ለማግኘት መታቀዱን አስረድተዋል።
የማሳ ሽፋኑን በማሳደግ ሂደት ከዚህ በፊት ሢሠራባቸው በነበሩ አካባቢዎች አዳዲስ መሬት ለማልማት እና ከዚህ በፊት የሩዝ ምርት ወደሌለባቸው አካባቢዎች ልማቱን ለማስፋፋት እየተሠራ ነው ብለዋል። ከዚህ በፊት በምሥራቅ አማራ አንዳንድ አካባቢዎች የነበረው የአየር ሁኔታ ለሩዝ ምርት ምቹ መኾኑን ተከትሎ ሙከራ ሲደረግበት መቆየቱን ገልጸዋል።
ዘንድሮ በሰሜን ሸዋ አካባቢ እንዲሁም በደቡብ ወሎ ቃሉ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች ወደ ሩዝ ምርት እንዲገቡ የመሬት ልየታ እና የዘር ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን አስታውሰዋል። በክልሉ የሩዝ ሰብል በሁለት ዓይነት መልኩ እንደሚዘራ የተናገሩት አቶ ቃልኪዳን አንደኛው በመደበኛ አሠራር በውኃማ አካባቢዎች የሚለማ ሲኾን በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ 86 በመቶ የማሳ ሽፋን ካላቸው 10 አይነት የእህል አይነቶች ጋር በማካተት የሚለማበት ሁኔታ እንዳለ አስረድተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!