
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ምግብ ዋስትና ልማታዊ ሴፍትኔት ማስተባበሪያ በክልሉ በምግብ ዋስትና ልማታዊ ሴፍትኔት የተሠሩ ሥራዎችን በኮምቦልቻ ከተማ ገምግሟል፡፡ በግምገማው በክልሉ በምግብ ዋስትና ልማታዊ ሴፍትኔት የታቀፉ 18 ከተሞች የተሳተፉበት የሁለት ዓመት ተኩል ሥራ እና የ2017 ዕቅድ ቀርቧል።
የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሱለይማን እሸቱ እና በክልሉ በምግብ ዋስትና የታቀፉ የ18 ከተማ ተወካዮች በተገኙበት በኮምቦልቻ ከተማ በምግብ ዋስትና ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም የተሠሩ ተግባራት የመስክ ምልከታ ተካሂዷል። ምክትል ኀላፊ ሱለይማን እሸቱ በከተሞች የተጀመረው የምግብ ዋስትና ፕሮግራም የተጠቃሚዎችን ዘላቂ ኑሮ በማሻሻል እና የከተማን ገጽታ በመገንባት ረገድ ፋይዳው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል።
ፕሮግራሙን ውጤታማ ለማድረግ አሳታፊነት፣ የመሪዎች ቅርብ ክትትል፣ የሰው ኃይሉን አደረጃጀት ማጠናከር እና የመሬት አቅርቦት ማሳደግ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ቢሮው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ሱሎይማን አስረድተዋል። የአማራ ክልል ምግብ ዋስትና ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ ሀሰን ሙህዬ ከገጠር ወደ ከተሞች ፍልሰት በመኖሩ እና የድህነት መጠኑም ከፍተኛ በመኾኑ በምግብ ዋስትና ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ተመቻችቶ የተረጅነት መንፈስን በማስወገድ ሠርተው እንዲለወጡ የሚያግዝ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ከተሞች ያላቸውን ፀጋ በመለየት ተጠቃሚዎችን ከድህነት የሚወጡበትን እና ወደ ዘላቂ ኑሮ የሚሸጋገሩበትን አሠራር ማመቻቸት እንደሚገባም አብራርተዋል። የኮምቦልቻ ከተማ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው የሰቆጣ ከተማ ምግብ ዋስትና ልማታዊ ሴፍትኔት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዘሩ ጌታወይ እና የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የምግብ ዋስትና ልማታዊ ሴፍትኔት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እታፈራሁ አስግደው እንደገለጹት የከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራም መጀመሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች የቁጠባ እና የሥራ ባሕላቸው እንዲያድግ እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡ የአካባቢን ገጽታ በመገንባት ረገድም ሚናው የጎላ መኾኑን አብራርተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!