“አምኜ ገንዘቤን ተበላሁ”

16

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

ወይዘሮ ሰላም እርቄ ይባላሉ በባሕርዳር ከተማ አባይ ማዶ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው የሚኖሩት። በመንግሥት ሥራ ነው የሚተዳደሩት፡፡ በመንግሥት ሥራ ውስጥ ሲሠሩ በመሥሪያ ቤታቸው ውስጥ ያለን ኢንተር ኔት በመጠቀም የማኅበራዊ ሚዲያውን የመጠቀም እና የመከታተል ልምድ ነበራቸው፡፡
ወይዘሮ ሰላም እንደሚነግሩን አብዛኛውን በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቅ መረጃን ሙሉ በሙሉ እውነት አድርገው ያምኑ ነበር፡፡

ግለሰቧ ለአሚኮ ዲጅታል ሚዲያ በሰጡት አስተያየት አንድ ቀን እንደለመዱት ወደ ማኅበራዊ ሚዲያው ገብተው ሲመለከቱ አንድ ቀልባቸውን የሳበ ጉዳይ ይመለከታሉ፡፡ “በቀላሉ ከቤተዎ ቁጭ ብለው በስልክዎ ገንዝብ የሚሠሩበትን መላ ዘይደናል ይህን ያውቃሉ?” የሚሉ ማስታወቂያዎችን ይመለከታሉ።
ወትሮውንም ቢኾን የማኅበራዊ ሚዲያውን የሚያምኑት ወይዘሮ ሰላም በቀጥታ ባስቀመጡላቸው ሊንክ በመግባት የሚጠየቁትን መረጃ በሙሉ ያስገባሉ፡፡

በኋላ ላይ አንድ ሰው የባንክ ሥራ አሥኪያጅ ነኝ በማለት ስልክ ይደውልላቸዋል። በተሳተፉት መሠረት 40 ሺህ ብር ማግኘተወን ለማረጋገጥ ነው የደወልኩት ይላቸዋል። ወይዘሮ ሰላምም በሰሙት ነገር ደስ ይላቸዋል። ምንም ክፉ ነገር ይገጥመኛል ብለው አላሰቡም። እሳቸውም የተጠየቁትን መረጃ ከሰጡ በኋላ ብራቸውን ሊያገኙ የሚችሉበትን ባንክ ይጠይቃሉ፡፡ የደወለላቸው ሰውም የአምስት መቶ ብር ካርድ እንዲልኩ እና በቀጥታ የባንክ አካውንታቸው ወዳለበት ቦታ ከአንድ ቀን በኋላ እንዲሄዱ ነግሯቸው ተመሠጋግነው ስልኩን ይዘጋሉ፡፡

ወይዘሮ ሰላም ካርድ ገዝተው ቁጥሩን በተባሉበት ስልክ ላኩ፡፡ ይህ እስኪኾን ምንም ጥርጣሬ አልነበራቸውም፡፡ በሚቀጥለው ቀን ወደ ተባሉት ባንክ ቤት ሲሄዱ ግን የፈለጉት ሳይኾን ያላሰቡት ገጠማቸው፡፡ ገንዘባቸውንም እንደተበሉ እና ሀሰተኛ መረጃ እንደኾነም የተገለጠላቸው ያኔ ነበር፡፡ ያልጠረጠረ ተመነጠረ… ለዘገባችን መነሻ ወይዘሮ ሰላምን አነሳን እንጅ በርካቶች በዚሁ እና በሌሎች መንግዶች ገንዘባቸውን ተበልተዋል፡፡

እኛም የወይዘሮ ሰላምን ታሪክ በማንሳት ለረዥም ጊዜ በእውነት ማጣሪያ አሠልጣኝ እና የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ የኾኑትን አብነት ቢኾነኝ ስለማጭበርበር ወንጀል እና ስለ መከላከያ መንገዶች ጠይቀናቸዋል፡፡ ባለሙያው እንደሚሉት የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት በገንዘብ ተቋማት ብቻ ሳይኾን አጠቃላይ ማኅበራዊ ሚዲያው የፈጠረው ችግር መኾኑን ይገልጻሉ፡፡

ማኅበራዊ ሚዲያው ከሌላው በተለየ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ከፍ እንዲል እንደሚያደርግ ነው የነገሩን፡፡ የማኀበራዊ ሚዲያ መረጃዎች በቀላሉ ሰዎች ላይ እንዲደርስ ዕድል የሚፈጥር በመኾኑ ችግሩን ያከፋዋል ብለዋል፡፡ ወይዘሮ ሰለምን የገጠመው አይነት ማጭበርበር ኾን ብሎ ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ላይ እንደሚመደብ ነው የሚገልጹት፡፡

ሌሎች የሀሰተኛ መረጃ ስርጭቶች በመጠኑ ይዘታቸው እንዲቀየር ተደርጎ እንዲሰራጩ የሚደረግ ሲኾን ይህኛው ግን ሙሉ ለሙሉ የፈጠራ የኾነ ሀሰተኛ መረጃ ስለመኾኑ ነው ያብራሩት፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የሚለቀቁ ነገሮችን የመረጃ ማጣሪያን ተጠቅመው ሳያጣሩ መጠቀም ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ነው የሚናገሩት፡፡

መረጃው ሲጣራ እንደማንኛውም የመረጃ ማጣራት መንገድ ተጠቅሞ ማጣራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ለየት ያሉ ፎቶዎች እና ቪዲዮች ሲኾኑ በማጣሪያ መንገዶች ተከትሎ ፎቶውን እያስገቡ ትክክለኛነቱን ማጣራት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ባንኮች ከሚሰጡት መመሪያ ውጭ በስልክ የሚፈጸም አሠራር ስለሌለ ከባንክ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ በስልክ ለሚጠየቅ መረጃ ምላሽ አለመስጠት እንደሚመከር ነው ያብራሩት፡፡

ምናልባትም መረጃውን ከመስጠታቸው በፊት ወደ ባንኮች ሄደው ማጣራት እንዳለባቸውም አስረድተዋል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ ከኾነ ምንጩን ማየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ባለቤቱ ማነው? የሚታወቅ ነው? የሚለውን መለየት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ሌላው ማኅበራዊ ሚዲያው መቼ እንደተከፈተ ቀኑን ማየት ያስፈልጋል። ምክንያቱም የተለቀቀው መረጃ ከዚህ በፊት ሽልማት እንደሚሰጥ አንድ ታዋቂ ድርጅት የተጠቀመበትን መረጃ ለረዥም ጊዜ እያዟዟሩ ሊጠቀሙት ስለሚችሉ ይህንንም መለየት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ሀሰተኛ መረጃ ነው ተብሎ የተጠረጠረውን መረጃ “ሎኬሽን” ወይም ያለበትን አድራሻ በመለየትም ማወቅ እንደሚቻል ነው የሚገልጹት። ምክንያቱም ጉዳዩ ሀገር ውስጥ ይኾን እና የተለቀቀበት ማኅበራዊ ሚዲያ አድራሻ ከሀገር ውጭ ስለሚኾን ነው ያሉት፡፡ የተለጠፈው ልጥፍ ፍላጎቱ ምንድን ነው? እውነት መረጃ ለመስጠት እና ለመጥቀም ነው? የሚለውን መለየት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ግለሰቧም ይህን የማጣራት ሂደት ሳያልፉ ሁሉ ነገር እውነት ነው ብለው በማመናቸው የመጣ ጉዳት እንደኾነ የገለጹት ባለሙያው ከፋይናንስ ተቋማት እንደዚህ አይነት መረጃ ፈጽሞ ተደውሎ ስለማይጠየቅ ችግሩ የተፈጠረው ይህን ካለማወቅ የመጣ እንደኾነ ነው ያብራሩት፡፡ ባንኮች ቢፈልጉ እንኳን ቅርብ ወደ ኾነ ቅርንጫፍ እንዲመጡ መልዕክት ከማስተላለፍ ውጭ ግለሰቦችን በስልክ መረጃ እንደማይጠይቁም ተናግረዋል፡፡

እንዲህ አይነት ጥያቄ ሲመጣም መረጃ ከመስጠት በፊት በሚቀርብ የተቋሙ ቅርንጫፍ በመገኘት ማጣራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በማኅበራዊ ገጹ ላይ እንዳለው ደግሞ አንዳንድ ግለሰቦች እና የወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎች የተለያየ ገጽታ ያላቸው ወንጀሎችን በመፈጸም በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ለማግኘት እንቅስቃሴ እያደረጉ መኾኑን መረጃ እንደደረሰው ገልጿል፡፡

የኦንላይን እና ልዩ ልዩ ማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም የትርፍ ጊዜ ሥራ፣ አማራጭ እና አዋጭ ሥራ እንዲሁም ኢንቨስትመንት የሚል ማደናገሪያ ስልቶችን በመጠቀም ግለሰቦችን በኦንላይን በመቅረብ እና ግንኙነት በመፍጠር ወደ ማጭበርበሪያ ሰንሰለት ውስጥ በማስገባት ገንዘብ ወስደው ሲሰወሩ መቆታቸውን አስታውሷል።

በኦንላይን እና ማኅበራዊ ሚዲያ የማጭበርበር ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት ሀሰተኛ ስም እና አድራሻ በመጠቀም እንዲሁም መቀመጫውን በውጭ ሀገራት አድርገው በአንዳንድ መሰል ድርጊት ላይ ከተሰማሩ ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር የወንጀል ድርጊቱን ሲፈጽሙ የነበሩ ናቸው ብሏል። እነዚህ አካላት በውጭ ሀገራት ያሠባሠቡትን ገንዘብ በሀገር ውስጥ የወንጀል ድርጊቱ ተባባሪ በኾኑ ግለሰቦች አማካኝነት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በኢትዮጵያ ብር ለተለያዩ ግለሰቦች እንዲከፈል እና ተመጣጣኝ መጠን ያለው ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ እንደሚከፍሉ በማግባባት የውጭ ሀገራት ምንዛሪን ይዘው የመሰወር የወንጀል ድርጊት እንደሚፈጽሙም ገልጿል፡፡

እነዚህ አካላት በሕገ ወጥ ገንዘብ ምንዛሪ ላይ በመሰማራት የወንጀል ድርጊት ከመፈጸም ባሻገር የውጭ ሀገር ምንዛሬውን ይዘው በመሰወር በአንድ በኩል በግለሰቦች ላይ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ በሕጋዊ መንገድ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ በማሳጣት ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛሉ ብሏል።
ስለኾነም ኅብረተሰቡ የማጭበርበር እና መሰል የወንጀል ድርጊት ሰለባ እንዳይኾን እንዲጠነቀቅ አገልግሎቱ አሳስቦ መሰል የወንጀል ድርጊቶች ጋር ግንኙነት ያለው አጠራጣሪ ጉዳይ ሲመለከት በስልክ ቁጥር +251-11-812-8261 ወይም በአካል በመገኘት ጥቆማ እንዲሰጥ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleራስን በራስ የማልማት አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) አሳሰቡ።
Next article“በከተሞች የተጀመረው የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ኑሮ በማሻሻል እና የከተማን ገጽታ በመገንባት ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው” የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ