ራስን በራስ የማልማት አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) አሳሰቡ።

64

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማኅበራዊ ጥበቃ ምክር ቤት ምሰረታን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) እንዳሉት የማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲው በሁሉም ዘርፎች የሚመነጨውን ሀብት በማሳደግ ማኅበራዊ ጥበቃን ማረጋገጥ አላማ ያደረገ ነው።

ለችግር ተጋላጭ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መጠበቅ፣ ለአደጋ ከተጋለጡም የሕግ እና ማኅበራዊ ድጋፍ ማድረገ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል። ማኅበራዊ መድኅን በመስጠት ከተለያዩ ችግሮች መከላከል፣ ምጣኔ ሃብታዊ አቅማቸውን የሚያሳድጉበት የሥራ አማራጭ መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ምክንያት የሚደርሰው የተጋላጭነት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ያነሱት ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቋቋም ራስን በራስ በማልማት ሀብት መፍጠር እና ሀብቱን ማሥተዳደር የሚያስችል አሠራር እና አደረጃጀት መዘርጋት እንደሚገባም አንስተዋል።

ዜጎችን ፍትሐዊ የሀብት ተጠቃሚ ማድረግ ከተቻለ የማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ዋና ዓላማ የኾነውን ምርታማነት ማሳደግ እና በራስ አቅም የራስን ችግር መፍታት አስፈላጊ መኾኑንም አንስተዋል። የህጻናትን ተጎጅነት እና ብዝበዛን መቀነስ፣ ከኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማት ባለፈ የሰብዓዊ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይገባል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የቦርከና ወንዝ ድልድይ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው” የደቡብ ወሎ ዞን
Next article“አምኜ ገንዘቤን ተበላሁ”