“የቦርከና ወንዝ ድልድይ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው” የደቡብ ወሎ ዞን

18

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በቃሉ ወረዳ እየተገነባ የሚገኘው የቦርከና ወንዝ ድልድይ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን የደቡብ ወሎ ዞን መንገድ መምሪያ አስታውቋል፡፡ በአማራ ክልል የመንገድ ሽፋንን በማሳደግ የኅብረተሰቡን የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነቱን ለማጎልበት እየተሠራ ይገኛል፡፡

በዚህ ዓመት ከሚሠሩት የድልድይ ፕሮጀክቶች መካከል በአማራ ክልል መንግሥት ሙሉ ወጭ በ41 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር እየተገነባ የሚገኘው የቦርከና ወንዝ ድልድይ አንዱ ነው፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ ኢብራሂም ሀሰን ድልድዩ በዩራፕ መለኪያ ለዞኑ የመጀመሪያ ትልቁ ፕሮጀክት ስለመኾኑ ተናግረዋል፡፡

48 ሜትር ርዝመት፣ 8 ሜትር ከፈታ እንዲሁም 8 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት ያለው ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡ ግንባታው የካቲት 2016 ዓ.ም ተጀምሮ የነበረ ቢኾንም በተቋራጩ የመፈጸም ውስንነት ምክንያት ውሉ ተቋርጦ ለሌላ ተቋራጭ የክልሉ መንግሥት እንዲተላለፍ ማድረጉን አቶ ኢብራሂም ጠቁመዋል፡፡

ለአዲሱ ተቋራጭ ከተላለፈ በኋላ በሦስት ፈረቃ 24 ሰዓት በመሥራት በ25 ቀናት በርካታ ስራዎችን ማከናወን እንደተቻለም አመላክተዋል፡፡ በዚህም ሐምሌ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ግንባታው ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ በሚያስችል ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው፡፡ የዚህ ድልድይ መገንባት የኅብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ ከመመለስም ባሻገር ሀርቡ ከተማን፣ ሰሜን ሸዋን፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደርን፣ ሌሎች ቀበሌዎችን እና የወረዳ እንዲሁም የከተማ ማዕከላትን እንደሚያገናኝ አስረድተዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው አካባቢው ለማኅበራዊ አገልግሎት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር የአትክልት እና ፍራፍሬ ኮሪደር ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ለቀጣናው የምርት ዝውውር እና ኢኮኖሚ ልማት የላቀ ሚና እንደሚኖረውም አረጋግጠዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለችግር ተጋላጭ የኾኑ ዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተመሠረተው የማኅበራዊ ጥበቃ ምክር ቤት እስከ ቀበሌ ድረስ እንደሚዋቀር ተገለጸ።
Next articleራስን በራስ የማልማት አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) አሳሰቡ።