
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ተጋላጭ የማኀበረሰብ ክፍሎችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎች ተቀርጸው ሲተገበሩ ቆይተዋል፡፡ ተግባራዊ በተደረጉ ፖሊሲ እና ስትራቴጅዎች ተጠቃሚ ከኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች፣ ህጻናት፣ አረጋዊያን፣ አካል ጉዳተኞች እና በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ይገኙበታል።
የእነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የብሔራዊ ማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል። ሴፍቲኔት እና የማኅበራዊ መድንን ማስፋፋት፣ የመሠረታዊ አገልግሎቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንዲሁም ለጥቃት እና በደል ተጋላጭ ለኾኑ ዜጎች የሕግ ጥበቃ እና ድጋፍ መስጠት በማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲው የተቀመጡ የትኩረት መስኮች መኾናቸውን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ገልጸዋል።
ኀላፊዋ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት ተጋላጭ ዜጎችን የሴፍቲኔት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተችሏል፣ የጤና መድኅን አገልግሎት ተግባራዊ ተደርጓል፣ የትምህርት እና ጤና አገልግሎቶችን ተደራሽነት የማረጋገጥ ሥራ ተሠርቷል፣ የሦስተኛ ወገን መድኅን አገልግሎቶች ተግባራዊ ተደርገዋል። የጡረታ አገልግሎት በመንግሥት እና በግል ድርጅት ሠራተኞች ላይ ተግባራዊ መደረጉንም አንስተዋል።
ማኅበረሰቡ በማኅበረሰብ ድጋፍ እና እንክብካቤ ጥምረት፣ በእድር እና መሰል አደረጃጀቶች የሚያደርገው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል። ይሁን እንጅ የተጀመሩ ሥራዎች አሁንም ውጤት ሊያመጣ በሚችል መልኩ እየተመሩ አለመኾኑን አንስተዋል። በማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲው የተቀመጡ የትኩረት መስኮችን በተሟላ ሁኔታ በመተግበር የተለየ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ማኅበራዊ ጥበቃ ምክር ቤት ምሰረታ ማስፈለጉን አንስተዋል።
ይህንን አስመልክቶም ከመንግሥት ከፍተኛ ኅላፊዎች፣ ከማኅበረሰብ አደረጃጀቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የማኅበራዊ ጥበቃ ምክር ቤት ማስጀመሪ ውይይት ተካሂዷል። አደረጃጀቱ ከክልል አልፎ በዞን፣ በወረዳ እንዲሁም በሁሉም ቀበሌዎች የሚቋቋም እንደሚኾን ኀላፊዋ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!