“በጎነት እና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎ ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡

38

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሰላም ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመተባበር ‹‹በጎነት እና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ›› በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጀምሯል። በክረምቱ ወራት የሚከናወን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ንቅናቄ መርሐግብርን አስመልክተው የሦስቱ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና የብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ (ዶ.ር) ንቅናቄው “በጎነት እና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ያስጀመሩት ሀገራዊ ንቅናቄ መኾኑን ገልጸው “ሀገርና ሕዝብ በዜጎች ነጻ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚኾኑበት፣ ነባሩን የአብሮነት እና የመደጋገፍ ባሕላችንን የምናድስበት፣ ማኅበራዊ ግንኙነታችንን እና ብሔራዊ መግባባትን የምናጠናክርበት፣ ሀገርን በነጻ በማገልገል ከተለመደው ዓይነት አርበኝነት ለየት ያለ አርበኝነት የምንፈጽምበት ታላቅ ሀገራዊ ጥሪ እና ልዩ የኾነ ንቅናቄ ነው” ብለዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጦሽኔ “ለአብሮነት እሴት መሸርሸር ምክንያት የሚኾኑት አለመተዋወቅ እና አለመቀራረብ ስለኾኑ በዚህ የክረምቱ በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንሻገራለን” ብለዋል። ኢትዮጵያ ብዙ ወጣት ያላት ሀገር እንደመኾኗ ወጣቱን በስፋት ለማሳተፍ የተለመደው ዓይነት አሠራር ብቻ በቂ እንደማይኾን አስገንዝበው መሰል ንቅናቄዎችን መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ ሙና አሕመድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀገራችን የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው አንደነበር አንስተው በቅርቡ ደግሞ የተለየ ትኩረት እና ክትትል ተሰጥቶታል ነው ያሉት። ንቅናቄው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎችን ጨምሮ 40 ሚሊዮን በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ከ50 ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ አካላትን ተጠቃሚ የሚያደርግ መኾኑ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

ከሰላም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በክረምቱ ወራት በአረንጓዴ አሻራ፣ በቤት እድሳት፣ ለአረጋዊያን እና አቅመ ደካሞች ልዩ ልዩ ማኅበራዊ አገልግሎት መስጠት፣ በትምህርት እና በጤና ዘርፎች ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን በማገልገል ማኅበራዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበት መኾኑ ተነግሯል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዚዳንት ዴኒስ ፍራንሲስ ጋር ተወያዩ።
Next articleለችግር ተጋላጭ የኾኑ ዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተመሠረተው የማኅበራዊ ጥበቃ ምክር ቤት እስከ ቀበሌ ድረስ እንደሚዋቀር ተገለጸ።