አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዚዳንት ዴኒስ ፍራንሲስ ጋር ተወያዩ።

26

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዚዳንት ዴኒስ ፍራንሲስ ጋር ተወያይተዋል። ውይይታቸውም በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች እና በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የሰላም ማስከበር ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ መኾኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ የታዳጊ ሀገራት አጀንዳዎች በኾኑ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ የአቅም ግንባታ ድጋፎች እንዲሁም በዘላቂ ልማት ግቦች ማረጋገጥ ጉዳዮች ላይ እንደተወያዩ አንስተዋል። አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ኢትዮጵያ ለባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የምትሰጠውን ትልቅ ቦታ እንዲሁም በቀጣይ በሚካሄደው ‘summit of future’ የተሰኘውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ በተመለከተም ዝርዝር ውይይት ስለማድረጋቸው ጠቅሰዋል።

አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ በሚደረግ ጥረት እና መሰል የፀጥታ ጉዳዮችም የውይይቱ አካል መኾናቸውን ጠቅሰዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ዴኒስ ፍራንሲስ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምታደርገውን ጥረት ማድነቃቸውን ቃል አቀባዩ አንስተዋል። መንግስት ውስጣዊ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት የያዘውን ቁርጠኛ አቋምም ማድነቃቸውን እንዲሁ። ለልማት እንቅስቃሴዎችም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ስለመሆኑም አንስተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዳዲስ ምርቶችን ወደ ግብይት ሥርዓቱ ለማስገባት እየሠራ መኾኑን አስታወቀ።
Next article“በጎነት እና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎ ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡