የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዳዲስ ምርቶችን ወደ ግብይት ሥርዓቱ ለማስገባት እየሠራ መኾኑን አስታወቀ።

22

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2016 በጀት ዓመት 11 ወራት 23 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶች ማገበያየቱን ገልጿል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኃይሉ ንጉሴ ተቋሙ በሀገሪቱ ባሉት 25 ቅርንጫፎች ከ200 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምርት መቀበሉን ተናግረዋል።

በዚህም 23 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ማገበያየቱን ገልጸዋል። ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ቡና 18 በመቶ እንዲሁም የቅባት እህሎች 45 በመቶ ብልጫ እንዳላቸው እና ሌሎችም በተመሳሳይ እድገት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል። በአጠቃላይ አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ30 በመቶ እድገት አለው ነው ያሉት።

ምርት ገበያው አዳዲስ ምርቶችን ወደ ግብይት ሥርዓቱ ለማስገባት እየሠራ መኾኑን ጠቅሰው ለውጭ ገበያ የሚውሉ ባቄላ፣ ኑግ እና ሽንብራ በቅርቡ በግብይት ሥርዓቱ ያስገባቸው አዳዲስ ምርቶች መኾናቸውን ገልጸዋል። እነዚህን ምርቶች ከሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በምርት ገበያው እንዲሁም በውል እና ኢንቨስትመንት እርሻ በኩል ለማከናወን አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ተናግረዋል።

የቢራ ገብስ፣ ዳጉሳ፣ ተልባ፣ ቆዳ እና ሌጦ እንዲሁም የጥጥ ምርቶች ላይ ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው የቢራ ገብስን መቀበል የሚያስችል ጥናት ተጠናቆ የግብይት ውል መጽደቁን ተናግረዋል። በመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት 30 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ምርቶችን በመጋዘን በማከማቸት ከባንኮች ጋር ብድር የማመቻቸት ሥራ የተከናወነ ሲኾን ወደ 4 ሚሊዮን ብር ብድር መለቀቁን ጠቁመዋል።

የመጋዘን አገልግሎትን ለማስፋት የላብራቶሪ አቅምን በማደራጀት ከአንድ ምርት በላይ እንዲቀበሉ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል። ምርት ገበያው አገልግሎቱን ለማሳለጥ በከፈተው አካዳሚ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ እና በምርምር ዘርፍ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን ገልጸው አካዳሚው ለአፍሪካም የልህቀት ማዕከል ለመኾን እየሠራ ነው ብለዋል። ምርት ገበያው በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ግብይት የሚፈጽሙበት አሠራር ላይ የደረሰ ሲኾን በቀጣይ የተሻሉ አሰራሮችን ለመዘርጋት እየሠራ ይገኛል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበመኸር እርሻ 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ መኾኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስታወቀ።
Next articleአምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዚዳንት ዴኒስ ፍራንሲስ ጋር ተወያዩ።