ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የማዕድን ሀብት ለኃይል አማራጭ በመጠቀም የካርበን ልቀት ለመቀነስ እየሠራች እንደኾነ ተገለጸ።

29

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማትዮስ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍን ለኃይል አማራጭነት በመጠቀም የካርበን ልቀትን ለመቀነስ እየሠራች ትገኛለች። ኮፐር፣ ኒኬል፣ ኮባልት፣ ሊቲየም እንዲሁም ሌሎች ውድ እና ለኃይል አማራጭ የሚኾኑ የማዕድን አይነቶች በኢትዮጵያ የሚገኙ ስለመኾኑ በተለያዩ መንገዶች መረጋገጡን አመላክተዋል። ኢትዮጵያ ያላት ሀብት በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የደረሰውን የካርበን ልቀት ለመቀነስ ትልቁን ድርሻ እንድትወስድ ያስችላታል ሲሉ ገልጸዋል።

በኢኮኖሚው ረገድ የማዕድን ዘርፍ በቀጣይ የሀገሪቱን ልማት ከሚወስኑ ዘርፎች መካከል አንዱ እንዲኾን ያስችለዋል ሲሉ አብራርተዋል አቶ ሚሊዮን ። የማዕድን ልማት አቅጣጫው የካርበን ልቀት መቀነስ ላይ መሠረት ያደረገ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በዘርፉ ያሉ ጸጋዎችን በዘላቂነት መጠቀም ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር መኾኑን አብራርተዋል።

ከማዕድን ልማቱ ጎን ለጎን የተፈጥሮ ጋዝ እና የጂኦ- ተርማል ኃይልን ለተለያዩ ኃይል አማራጮች ለማልማት መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር እየሠራ ይገኛልም ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ይህን መሰል የልማት አቅጣጫ መከተል ከጀመረች ሦስት ዓመት አስቆጥራለች ያሉት አቶ ሚሊዮን የሚፈለጉት ማዕድናት በኢትዮጵያ የሚገኙ በመኾናቸው በዚሁ ዘርፍ ውጤታማ ለመኾን ከፍተኛ እድል መኖሩን አስረድተዋል።

አቶ ሚሊዮን እንዳሉት ኢትዮጵያ በአፍሪካ በማዕድን ልማት ላይ ከሚሠሩ የዘርፉ አልሚዎች ጋር በትብብር ለመሥራት ፍላጎት አላት። ኢፕድ እንደዘገበው ማዕድን አልሚዎቹ የሚያነሷቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር የሀገሪቱን ጥቅም ባስከበረ መልኩ ወደተግባር እንዲገባ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበመምህር እና ደራሲ እንደሻው ሽፈራው የተጻፈ ”አረህ እና አፋፍ” የተሰኘ ታሪካዊ ልብ ወለድ በባሕር ዳር ከተማ ተመረቀ።
Next articleተረጂነትን ወደ ታሪክ ሠሪነት