በመምህር እና ደራሲ እንደሻው ሽፈራው የተጻፈ ”አረህ እና አፋፍ” የተሰኘ ታሪካዊ ልብ ወለድ በባሕር ዳር ከተማ ተመረቀ።

27

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በመምህር እና ደራሲ እንደሻው ሽፈራው የተጻፈ ”አረህ እና አፋፍ” የተሰኘ ታሪካዊ ልብ ወለድ በባሕር ዳር ከተማ ተመርቋል። ልብ ወለድ መጽሐፉ በ18 ክፍል በ172 ገጽ ተሰናድቷል። ስለ ታሪካዊ ልብወለድ መጽሐፉ የዳሰሳ ትንተና ያደረጉት መምህር ዮሴፍ አያሌው ደራሲው ከልጅነቱ ጀምሮ ጥልቅ አንባቢ፣ ድንቅ ደራሲ፣ የታሪክ ተመራማሪ እና ተንታኝ ነው ብለዋል።

ደራሲው በድርሰቱ በሶሻሊስቱ እና በካፒታሊስቱ ጎራ በሚደረግ ሁለንተናዊ ፍልሚያ ውስጥ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እና ጽናትን እንዳሳየበት እና ከ1940 እስከ 50ዎቹ ያለውን ትውልድም እንዳንጸባረቀበት ተወስቷል። ደራሲው እንደሻው ሺፈራው የሥነ ጽሑፍ ታሪካችን ጥንታዊ እንደኾነ ተናግሯል። በማኅበረሰቡ ውስጥ እንደመኖሬ ለአፍ መፍቻ ቋንቋዬ ማደግ እኔም የበኩሌን ማበርከት ስላለብኝ “አረህ እና አፋፍ” የተሰኘ ሁለተኛ መጽሐፌን ለማስመረቅ ችያለሁ ብሏል።

ጥበብ እና ጥበበኛ በተትረፈረፈባት ሀገር ባለችኝ የቋንቋ አቅም ተጠቅሜ ይህቺን ትንሽ መጽሐፍ ሳበረክት እንደ ዜጋ የድርሻየን እንዳበረከትኩ ይሠማኛል ብሏል። ቤንጃሚን ፍራንክሊን ላለመረሳት ከፈለግህ ሊነበብ የሚችል ነገር ጻፍ አለበለዚያም ሊጻፍ የሚችል ታሪክ ሥራ ማለቱን ጠቅሶ ይህንን የሕይዎት መርህ በመከተል መጽሐፍ እንደሚጽፍ ነው የተናገረው። በቀጣይም አምስት ሥራዎችን ለተደራሲያን ለማቅረብ እቅድ እንዳለው ተናግሯል።

በአሁኑ ጊዜ ከመጽሐፍ ትርፍ የሚገኝ አለመኾኑን የሚገልጸው ደራሲ መምህር እንደሻው ትርፉ መጽሐፍ ከደራሲ ወጥቶ ለተደራሲ ሲደርስ የሚሰማው እርካታ ነው ብሏል። ልብ ወለድ ድርሰቱ በቅርቡ በሞት ለተለየኝ ልጄ ወጣት ናኦድ እንደሻው (ብሩክ) መታሰቢያ እንዲኾን በማድረጌም ደስ ብሎኛል ብሏል።

ለመጽሐፉ ምረቃ መሳካት ያገዙትን ሁሉ ያመሰገነው ደራሲ እንደሻው ሽፈራው በተለይ ለአማራ ልማት ማኅበር እና ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ምስጋናውን አቅርቧል። ልብ ወለዱ መጽሐፉን የመረቁት የአማራ ልማት ማኀበር (አልማ) ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አራጋው ታደሰ ደራሲው ለሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ለሚያበረክተው አስተዋጽኦ አመስግነው ማኅበረሰቡም የዘርፉን ባለሙያዎች ሊያበረታታ ይገባል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነት እና ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች” አቶ አደም ፋራህ
Next articleኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የማዕድን ሀብት ለኃይል አማራጭ በመጠቀም የካርበን ልቀት ለመቀነስ እየሠራች እንደኾነ ተገለጸ።