
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነት እና ትብብር በሁሉም ዘርፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
በአቶ አደም ፋራህ የተመራ የልዑክ ቡድን ከሰኔ 9 እስከ 12/2016 በሚካሄደው እና ዎርልድ ማጆሪቲ ፎር መልቲፖላር ኦርደር በሚል መሪ ቃል በሩሲያ ቪላዲቮስቶክ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ነው። ከፎረሙ ጎን ለጎን አቶ አደም ፋራህ ከቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ የዓለም አቀፍ ዘርፍ ሚኒስትር ሊዩ ጂንቻዎ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ላይ አቶ አደም ቻይና በኢትዮጵያ ልማት ላይ ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋር ሀገር መኾኗን አስረድተው በርካታ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜዎች ባጋጠሟት ፈተናዎች ሁሉ ቻይና የማይናወጥ አቋም ይዛ እያደረገች ላለው ድጋፍ ያመሰገኑት አቶ አደም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የፖለቲካ ወዳጅነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ባለው ብሪክስ አባል ሀገር ለመኾን ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲሳካ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲና መንግሥት ላደረጉት ድጋፍም አቶ አደም ምስጋና አቅርበዋል። አቶ አደም አያይዘውም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ስትራተጂያዊ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደምትሰራ ገልጸው ሊዩ ጂንቻዎን ጨምሮ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ አመራሮች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።
ሊዩ ጂንቻዎ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል በመኾኗ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነት እና ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ማዕከል በመኾኗም ቻይና ከኢትዮጵያም አልፎ ከአፍሪካዊያን ጋር ለሚኖራት ትብብር ቁልፍ ሚና እንዳላት አስረድተዋል።
በመኾኑም የሁለቱን ሀገራት የቆየ ትብብር ከማሳደግ ባለፈ የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቱን በልምድ ልውውጥ፣ በስልጠና ፕሮግራሞች እና በአቅም ግንባታ ዘርፍም አጠናክረው መቀጠል እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ከዚህ ባለፈም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ ቻይና በትኩረት እንደምትሰራ ገልጸው በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ትብብር የተገነባውን የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር በአብነት ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሩ በመጨረሻም በመጪው ጥቅምት በሚካሔደው የቻይና አፍሪካ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ልዑካን እንዲገኙ ግብዣ ማቅረባቸውን ኢዜአ ከስፍራው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!