የገንዳ ውኃ ወንዝ ድልድይ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን መንገድ መምሪያ አስታወቀ።

25

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዞኑ መንገድ መምሪያ ኀላፊ ዓባይነው ወረታው ከገንዳ ውኃ አቸራ የሚያገናኘው የገንዳ ውኃ ወንዝ ኮንክሬት ድልድይ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መኾኑን ተናግረዋል። ከክልሉ መንግሥት በተገኘ 35 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ከ50 ሺህ በላይ የኀብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

በዞኑ የኮንክሬት ድልድዮችን ጨምሮ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ መኾናቸውንም መምሪያ ኀላፊው ጠቁመዋል። በድልድይ ምረቃ ፕሮግራሙ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ቢክስ ወርቄ የዞኑ ማኀበረሰብ ለመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ እያደረገው ያለውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ አድንቀዋል።

ከአሁን በፊት የገንዳ ውኃ ወንዝ ድልድይ ባለመኖሩ በተለይም በክረምት ወቅት ምርታቸውን ወደገቢያ ለማምጣት እና ነብሰ ጡር እናቶችን ወደ ሆስፒታል ለማድረስ ይቸገሩ እንደነበር በመተማ ወረዳ የአቸራ፣ ከመቸላ እና ዘባጭ ባህር ቀበሌ ነዋሪዎች አስታውሰዋል። በ2013 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት ቢቆይም አሁን ላይ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መኾኑ ይደርስባቸው የነበረውን ማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደሚቀርፍላቸው ነው የገለጹት።

አሁን ላይ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች በታለመላቸው ጊዜ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡም ኀብረተሰቡ የተለመደ ድጋፍ እና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጉባኤ ቤቶች ታላቅ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ታላቅ ሀገርም አስረክበውናል” መምህር ሐረገወይን በሪሁን
Next article“ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነት እና ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች” አቶ አደም ፋራህ