“ጉባኤ ቤቶች ታላቅ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ታላቅ ሀገርም አስረክበውናል” መምህር ሐረገወይን በሪሁን

39

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቤተ ክርስቲያን ያስተማረቻቸውን ደቀመዛሙርት አስመርቃለች፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብክት የደብረ ዓባይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ጉባኤ ቤት ያስተማረቻቸውን ደቀመዛሙርት አስመርቃለች፡፡ ደቀመዛሙርቱ ብሉያትን፣ ሐደሲሳትን እና ቅኔን ተምረው ያጠናቀቁ ናቸው፡፡ ለዓመታት ትምህርትታቸውን ሲቀጽሉ የኖሩ ደቀመዛሙርት በአባቶቻቸው እግር ተተክተው የሚያስተምሩበትን የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

ብሉያትን እና ሐዲሳትን ተምረው የተመረቁት መምህር ዘላለም ድረስ በመጻሕፍት ትርጓሜ ብቁ ደቀመዛሙርት እየወጡ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ የጉባኤ ቤቱ መምህር ለደቀመዛሙርቶቻቸው የሚጨነቁ፣ ብቁ ደቀመዛሙርት እንዲወጡ የሚተጉ፣ ራሳቸውን ለደቀመዛሙርታቸው አሳልፈው የሚሰጡ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

ጉባኤ ቤት ባይኖር ኢትዮጵያ አይደለችም ዓለም በሙሉ አደጋ ላይ ትወድቃለች ነው ያሉት፡፡ በቅዳሴ ጊዜ ስለ ዓለም ይጸለያል፤ ጉባኤ ቤት ባይኖር የት ተምሮ ይጸለይ ነበር? ጉባኤ ቤት ከሌለ እውቀት የለም፣ ጥበብ የለም፣ የአንድ ቦታ መታወቂያ ጉባኤ ቤት ነው ይላሉ፡፡ ጉባኤ ቤቶች ምስጢር ይገለጥባቸዋል፤ ሀገርና ሃይማኖትም ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ጉባኤ ቤቶች ለነፍስም ለስጋም ታላቅ አስተዋጽዖ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

ሐዲሳትን እና ቅኔን ተምረው የተመረቁት መምህር ሕዝቅኤል አጠቃ ጉባኤ ቤት ለዓለም ጥበብን ሰጥታለች፤ እውቀትን መግባለች፤ ጉባኤ ቤት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለዓለምም መልካሙን ነገር የሰጠች ናት ብለዋል፡፡ ጉባኤ ቤት ምስጢርን እያመሰጠረች፣ እውቀትን እያነጠረች፣ ታላቅ ታሪክ ያላት ታላቅ ሀገር እንድትኖር አድርጓል ይላሉ፡፡ ጉባኤ ቤት መሠረት ነውና ሁሉም ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል፤ ወደ ቤተ ጉባኤ መቅረብ አለበት ብለዋል፡፡ እግዚአብሔር የመሠረተውን ጉባኤ ቤት ከአባቶቻችን ተቀብለን በእርሱ ፈቃድ ለልጆቻችን ለማስተላለፍ እንበረታለን ነው ያሉት፡፡

ደቀመዛሙርቱን አስተምረው ለምረቃ ያበቁት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ሰብከት የደብረ ዓባይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር መምህር ሐረገወይን በሪሁን የጉባኤ ቤት መሥራቹ ራሱ እግዚአብሔር ነው ብለዋል፡፡ በእግዚአብሔር መምህርነት፣ በሙሴ ደቀመዝሙርነት ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡ ከሙሴ በኋላ የመጡ አበውም ያስተምሩ ነበር፡፡ የጠፋውን የሰው ልጅ ለመፈለግ ወደ ምድር የመጣው ክርስቶስም ሐዋርያትን ያስተምራቸው እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡

ሐዋርያትን ምሳሌ መስሎ፣ ትርጓሜ አመስጥሮ፣ ሚስጥር አስረድቶ ያስተምራቸው ነበር ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር የጀመረውን ጉባኤ በመከተል ልጆቿን ስታስተምር የኖረች አሁንም ጉባኤ ቤት ዘርግታ እያስተማረች ያለች፣ ወደፊትም የምታስተምር መኾኗን ነው የተናገሩት፡፡

ጉባኤ ቤቶች የእውቀት እና የፍልስፍና መፍለቂያ መኾናቸውን ያነሱት መምህር ሐረገወይን ለዓለም እና ለቤተክርስቲያን ያደረገችው አስተዋጽዖ የላቀ ነው ብለዋል፡፡ ጉባኤ ቤቶች ለቤተክርስቲያን እስትንፋስ ናቸው ነው ያሉት፡፡ ቤተክርስቲያን ያለ ጉባኤ ቤት መኖር አትችልም፣ ኖራም አታውቅም ብለዋል፡፡ በጉባኤ ቤት ዲያቆናት፣ ቀሳውስት፣ ሊቃውንት፣ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡ ቤተክርስቲያኗን ከፍ የሚያደርጉ መምህራን የሚፈጠሩትም ከጉባኤ ቤት መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ዶግማዋ ሳይፈርስ፣ ቀኖናዋ ሳይጣስ ሥርዓተ አምልኮዋ ሳይለወጥ፣ ከእነ ሙሉ ክብሯ እና ማንነቷ ከዚህ የደረሰችውም በጉባኤ ቤት ነው ብለዋል፡፡ የቤተክርስቲያን ጉልላት እና መሠረት ለኾኑት ጉባኤ ቤቶች ሁሉም ድጋፍ ሊደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ጉባኤ ቤቶች ሙሉ ማንነት ያላት ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ሙሉ ማንነት ያላት ሀገርም ያስረከቡን ናቸው ብለዋል፡፡ ጉባኤ ቤቶች ለኢትዮጵያ ቋንቋን ከነፊደሉ፣ ሥነ ጽሑፍን ከእነ አመሉ፣ ዜማን ከእነ ምልክቱ፣ የሥነ ከዋክብት ቀመርን፣ የአስተዳደር ሕግን ከእነሴቱ ማስረከባቸውንም ተናግረዋል፡፡ ጉባኤ ቤቶች ታላቅ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ታላቅ ሀገርም አስረክበውናል ነው ያሉት፡፡

ለሀገር ታላቅ ውለታ ያበረከቱት ጉባኤ ቤቶች ተዘንግተው ደጋፊ እንዳጡም ገልጸዋል፡፡ የተዳከሙ እና የጠፉ ጉባኤ ቤቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ ክርስቲያኖች ጉባኤ ቤቶችን መጠበቅ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡ የደብረ ዓባይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የመጻሕፍት ትርጓሜ ጉባኤ ቤትም በርካታ ደቀመዛሙርትን እያወጣ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ጉባኤ ቤቱ በሃሳብም፣ በሥነ ልቡና፣ በትምህርትም ቀድመው የሚመሩ ደቀመዛሙርት እንዲኖሩ እንደሚያስተምርም ገልጸዋል፡፡ የተመረቁ ደቀመዛሙርት ትውልዱን በሥነ ልቡና፣ በመንፈስ የማነጽ፣ ከችግሮች መውጫ መንገድ የማመላከት፣ ሰውን ሰው የማድረግ፣ ምግባር እንዲሠራ ሃይማኖት እንዲማር የማድረግ ኀላፊነት አለባቸው ነው ያሉት፡፡

ደቀመዛሙርቱ ትውልዱ ሀገሩን፣ ሃይማኖቱን፣ እሴቱን፣ ትውፊቱን እንዲጠብቅ እንዲደርጉ መንፈሳዊውን ሕይዎት ከስጋዊ ጋር አጣምረው እንዲይዙ ተደርገው እንደሚቀረጹም ገልጸዋል፡፡ ጉባኤ ቤቶች የመማሪያ ቦታ፣ የመኖሪያ ቤት እና ሌሎች ችግሮች እንዳሉባቸውም ገልጸዋል፡፡ ጉባኤ ቤቱ እንዲጠናከር ሁሉም ድጋፍ እንዲደርግም ጠይቀዋል፡፡ ከሁሉም የላቀችውን ጥበብን የፈለጉ ደቀመዛሙርት የተቀበሉትን አደራ በሚገባ እንዲወጡ አደራ ብለዋል፡፡ ሀገር እና ቤተክርስቲያንን በሚያሻግር ስሙር ተግባር እንድትኖሩ አደራ ጥየባችኋለሁ ነው ያሏቸው፡፡

የደብረ ዓባይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አስተዳደሪ መላከ ብርሃን ቆሞስ አባ ክፍለ ማርያም ዓለማየሁ ቤተክርስቲያን ልጇቿን አስተምራ፣ መርቃ፣ ያልጣፈጠውን ዓለም እንዲያጣፍጡ፣ አልጫ ለኾነው ዓለም ጨው እንዲኾኑ በአጽናፍ ዓለም እየዞራችሁ አስተምሩ ብላ መክራ ክብርን ሰጥታለች ብለዋል፡፡

ቤተክርስቲያን የሰጠቻቸውን ኀላፊነት በአግባቡ እንዲጠብቁም አደራ ብለዋቸዋል፡፡ ፈተናዎችን ሁሉ በጽናት እያለፉ መልካሙን ነገር እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ የጉባኤ ቤቱ እንዲሠፋ ቤተክርስቲያኗ እንደምትሠራም አስታውቀዋል፡፡ ጉባኤ ቤቱ የተመቻቸ የመማሪያ ቤት እንዲኖረውም ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መላከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁን ቤተክርስቲያን በመከራ፣ በፈተና ውስጥ እያለፈች ትቀጥላለች ብለዋል፡፡ ልጆችን ወደ አብነት ትምህርት ቤት በመላክ መንፈሳዊ ትምህርትን እንዲማሩ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሀገር እንዲጥቅሙ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ መጪውን ዘመን አስቦ ቤተ ጉባኤዎዎችን መደገፍ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ቤተ ጉባኤ የሊቃውንት መፍለቂያ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዘምዘም ውኃ!
Next articleየገንዳ ውኃ ወንዝ ድልድይ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን መንገድ መምሪያ አስታወቀ።