የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓልን ምክንያት በማድረግ ለከፋ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ።

21

ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

ምርኩዝ የልማት፣ የትምህርት እና የማኅበራዊ ድጋፍ በጎ አድራጎት ማኅበር 1 ሺህ 445 ኛውን የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል ምክንያት በማድረግ ለከፋ ችግር ለተጋለጡ ለእስልምና እና ለክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ድጋፍ አደረገ።

በአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ አንዋር እንዳሉት የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል የእድሜ ፣የጾታ፣ የብሔር፣ የዘር፣ የቋንቋ፣ የቀለም ልዩነት ሳይኖር ሁሉም በአንድነት እንዲሁም በትብብር የሚከበር የደስታ ቀን ነው ብለዋል። በዓሉ ለመጭው ወራትም ስንቅ የሚያዝበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም በዚህ እሳቤ መሠረት በባሕር ዳር ከተማ ለሚኖሩ ከ300 በላይ ለከፋ ችግር ለተጋለጡ፣ አቅመ ደካሞች እና ወላጆቻቸውን ላጡ የእስልምና እና የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ሕጻናት ልዩ ልዩ ድጋፎች ተደርገዋል ብለዋል።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሼህ አብዱርሃማን ሱልጣን በበኩላቸው ምርኩዝ የልማት፣ የትምህርት እና የማኅበራዊ ድጋፍ በጎ አድራጎት ማኅበር ምስኪኖችን በዒድ የበዓል ቀን ተደስተው እንዲውሉ በማሰብ የምግብ ዘይት፣ የምግብ ዱቄት እና የሥጋ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

ዋና ጸሐፊው እንዳሉት ለከፋ ችግር ለተዳረጉ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮችም የራሳቸውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በጠበቀ መልኩ በሬ በመግዛት ሥጋ እንዲከፋፈሉ ተደርጓል ብለዋል። ይህ መሰሉ ሠናይ ምግባር ሊመሰገን፣ ሊበረታታ እና ሊደገፍም ይገባዋል ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው።

የምርኩዝ የልማት፣ የትምህርት እና የማኅበራዊ ድጋፍ በጎ አድራጎት ማኅበር ፕሬዝዳንት ኡስማን ኑርልኝ ለ303 ለከፋ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች የምግብ ዘይት፣ ሥጋ እና የምግብ ዱቄት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ለክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ምስኪኖችም በ44 ሺህ ብር ወጭ በሬ በመግዛት ሥጋውን ማከፋፈላቸው ነው የተናገሩት።

ድጋፍ ከተደረገላቸው የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ አንዱ አቶ ሀብታሙ ይታያው “ምርኩዝ በየወሩ በቋሚነት የ700 ብር ድጋፍ ያደርግልኛ፤ ዛሬ ደግሞ ሥጋ ሰጥቶኛል” ብለዋል።

በሌላ በኩል አካል ጉዳተኛዋ ወይዘሮ ሞሚና ሙሐመድ “ዛሬ ዘይት፣ የፊኖ ዱቄት እና ሥጋ ተለግሶኛል” ካሉ በኋላ ምርኩዝን አመስግነዋል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀጂ ማድረግ ምድራዊዋን እና የመጀመሪያዋን የፈጣሪ ቤት መጎብኘት ነው”
Next articleየዘምዘም ውኃ!