
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ 75 በመቶ የሚኾነው አካባቢ ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ እንደነበር ልዩ ልዩ መዛግብት ይጠቁማሉ፡፡
የሀገሪቱ 60 በመቶ የሚኾነው ሕዝብም ለበሽታው ተጋልጦ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
በኢትዮጵያ በዋነኛነት የወባ በሽታ የሚተላለፍበት ወቅት በክረምት ቢኾንም በ1960ዎቹ ግን በወቅት የተገደበ አልነበረም፡፡ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴም በሽታውን አስቀድሞ መከላከል ካልተቻለ ከግብርናው ሥራ ጋር በተያያዘ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያመጣል ሲሉ በየጠቅላይ ግዛቱ እየተዟዟሩ ከሹማምቶቻቸው ጋር መከሩ፡፡
የጠቅላይ ግዛቶቹ ሹማምቶች ደግሞ ኅብረተሰቡን እንዲያነቁ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ በዚህ መሠረት በሽታውን ለመቆጣጠር ማኅበረሰቡ በወባ መከላከል ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ጥረት ተደረገ፡፡ ነገር ግን የተባለው ቢኾንም የበሽታው ስርጭት መግታት ሳይቻል ቀረ፤ በመኾኑም ንጉሠ ነገሥቱ የውጭ ሀገር እገዛን ጠየቁ፡፡
በዚህም መሠረት ፊታቸውን ወደ አሜሪካ አዞሩ፡፡ አሜሪካም የንጉሡን ጥያቄ በአዎንታ መቀበሏን አሳወቀች፡፡ ሰኔ 2 ቀን 1963 ዓ.ም አሜሪካ በኢትዮጵያ ለበርካቶች ሞት ምክንያት የኾነውን የወባ በሽታ ለማጥፋት ፈር ቀዳጅ ስምምነት አደረገች፡፡
በስምምነቱ መሠረትም አሜሪካ የሐኪሞች ቡድን አስቀድማ ላከች፡፡ መድኃኒት እና ለወባ ትንኝ ማጥፊያ ግልጋሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎችን ኢትዮጵያ ውስጥ አስገብታ ሥራ ላይ አዋለች፡፡
በአሜሪካ ዘርፈ ብዙ ድጋፍም ኢትዮጵያ ውስጥ የወባ በሽታ ስርጭትን በመቆጣጠር የበርካቶችን ሕይዎት መታደግ ተችሏል፡፡ “ማላሪያ ጆርናል ኢን ኢትዮጵያ ” መጽሐፍን በምንጭነት ተጠቅመናል፡፡
———–//////———//////———–/////
የነጻነት ተምሳሌቱ
ሮሊላሂላ ማንዴላ የተወለዱት ትራንስኪ በተባለው የደቡብ አፍሪካ ከተማ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ918 ነበር።
ማንዴላ በ25 ዓመታቸው በፎርት ሃሬ ዩኒቨርሲቲ እና በዊትዋተርስራንድ ዩኒቨርሲቲ ተምረው በሕግ ተመርቀዋል። ከመጀመሪያ ባለቤታቸውም አራት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ በ1958 ከባለቤታቸው ጋር ተለያይተውም ፊታቸውን ወደ ትግሉ በማዞር የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መኾን ጀመሩ።
ማንዴላ በ1952 የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳት በመኾን የአፓርታይድ ሥርዓትን በጽኑ መታገል ጀመሩ። ይህ በዚህ እንዳለ በ1956 ማንዴላ በሀገር ክህደት ወንጀል በጊዜው በነበረው የነጮች መንግሥት ተከስሰው አምስት ዓመት ያህል በክርክር ከቆዩ በኋላ በክርክሩ አሸነፉ።
የወቅቱ መንግሥት በ1960 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ እንቅስቃሴ ሲከለክል ማንዴላ በበኩላቸው ሰላማዊ ትግል እንደማያዋጣ በማመን ልዩ የጦር ኃይል አደራጁ። እርሳቸውም የጦሩ የበላይ አዛዥ በመኾን እርዳታ ፍለጋ ወደሌሎች ሀገራት ጉዞ ማድረግ ጀመሩ። ከውጭ ሀገር ሲመለሱ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተያዙና አምስት ዓመት እስር ተፈረደባቸው።
በ1963 እንደገና ማንዴላ እና ሌሎች የ ኤ ኤን ሲ መሪዎች መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ የሚል ክስ ተከፈተባቸው እና ፍርድ ቤት ቀረቡ። ከዚያም ዕድሜ ይፍታህ ተፈረደባቸው እና ሮቢን ደሴት እስር ቤት ተላኩ። ከሮቢን ደሴት ሌላ በተዘዋወሩባቸው ተጨማሪ እስር ቤቶችም በጠቅላላው 27 ዓመታት በእስር ሲቆዩ ትግላቸውን አጠናክረው በመቀጠላቸው እና ሌሎችም የእርሳቸውን ፈለግ በመከተላቸው በመላው ዓለም የነጻነት ምሳሌ ተደርገው ተወሰዱ ዝናቸውም እየሰፋ መጣ።
በ1990 ዓ.ም የደቡብ አፍሪካ የነጮች መንግሥት በተደረገበት ዓለም አቀፍ ጫና ማንዴላን ከእስር ፈታቸው። ኤ ኤን ሲ የተባለው ድርጅታቸውም እንዲንቀሳቀስ ተፈቀደላቸው – ማንዴላም ተመልሰው ሊቀመንበርም ኾኑ።
ማንዴላ እና የዚያን ጊዜው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኤፍ ደብሊው ደ ክላርክ በጋራ የዓለም የሰላም የኖቤል ሽልማት ተሸለሙ። ይህም የኾነው ጥቁሩ ማንዴላ እና ነጩ ደ ክላርክ የአፓርታይድ ሥር ዓትን ለማጥፋት ቁርጠኛ ስምምነት በማድረጋቸው ነበር።
በ1994 ደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያውን ነጻ ምርጫ አደረገች እና ማንዴላ የሀገሪቷ የመጀመሪያ ጥቁር ፕሬዚዳንት ኾኑ።
በ2004 ማንዴላ ከፖሊቲካው ራሳቸውን አራቁና ጡረታ መውጣታቸውን አስታወቁ። እንዲያውም ያን ጊዜ “ለማውቃችሁ ሁሉ እኔ እደውልላችኋለሁ እንጂ እናንተ እንዳትደውሉልኝ” ማለታቸው ይነገርላቸዋል።
እኝህ የነጻነት ተምሳሌቱ ኔልሰን ማንዴላ የዕድሜ ልክ እስራት የተበየነባቸው በያዝነው ሳምንት ሰኔ 5/1956 እንደነበር ታሪክ ያስታውሰናል፡፡ የመረጃ ምንጫችን በአትላንታ የታተመው ድንቅ መጽሔት መኾኑን ልብ ይሏል፡፡
——–/////——-//////——-/////——
የመጀመሪያዋ ጠፈርተኛ
ቫለንቲና ቭላዲሚሮቭና ቴሬሽኮቫ ትባላለች፡፡ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1937 ማስሌኒኮቮ ሩሲያ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ተወለደች፡፡
እናታቸው የጨርቃ ጨርቅ ሠራተኛ፣ አባቷ ደግሞ የትራክተር ሹፌር ነበሩ፡፡
ቫለንቲና ቴሬሽኮቫ በ18 ዓመቷ በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ መሥራት ጀመረች፡፡ ከሥራዋ ጎን ለጎንም “ሠማይ ዳይቪንግ እና ፓራሹቲስት ክለብ” ተቀላቀለች፡፡ በክለቡ ውስጥ የመጀመሪያዋ የመብረር ፍላጎት በማሳየቷ አድናቆት ተቸራት፡፡
ቫለንቲና በ22 ዓመቷ የመጀመሪያውን የፓራሹት ዝላይ አደረገች፡፡
ቀስበቀስም የሶቪየት የህዋ መርሐ ግብር ኮሚቴም ቫለንቲና ቴሬሽኮቫን ከአውሮፕላን ላይ ከመዝለል ባሻገር ወደ ጠፈር እንድትበር ጥያቄ አቀረበላት፡፡ የእርሷ ምላሽም አዎንታዊ በመኾኑ ከ400 እጩ ጠፈርተኞች መካከል በግንባር ቀደምትነት ተመረጠች፡፡
ቴሬሽኮቫ ከተመረጠች በኋላ በሶቪየት አየር ኀይል ውስጥ የ 18 ወራት ከባድ ሥልጠና ተሰጥቷታል፡፡
በ 24 ዓመቷም ወደ ሶቪየት አየር ኀይል በክብር ተቀላቀለች፡፡ ቴሬሽኮቫ በህዋ ላይ ለመብረር የመጀመሪያዋ ሲቪል ሰው መኾኗን የሚፈቅድ የምስክር ወረቀት ተሰጣት፡፡
የመጀመሪያዋ ጠፈርተኛ ቫለንቲና ቭላዲሚሮቭና ቴሬሽኮቫ ቮስቶክ አምስት በተሰኘ መንኮራኮር ወደ ጠፈር የመጠቀችው በዚህ ሳምንት ሰኔ 8 ቀን 1955 ዓ.ም ነበር፡፡
ቫለንቲና ቴሬሽኮቫ ወደ ጠፈር ስትመጥቅ የሶቪየት ኅብረት ቴሌቭዥን በቀጥታ ለዓለም ሕዝብ ያሰራጭ ስለነበር የዓለምን ሕዝብ አጃኢብ አሰኝቷል፡፡ ጠፈርተኛዋ በወቅቱ የሩሲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት ኒኪታ ክሩሽቼቭ ጋር በራዲዮ ትገናኝ ነበር፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!