በነብያቶች የተጎበኘችው ቅዱስ ከተማ – መካ

33

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የትውልድ ሥፍራ ናት ፤ በነብዩ ኢብራሂም እንደተመሠረተችም ይነገራል። በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ቅዱሷ ከተማ እየተባለች ትጠራለች ፤ በምዕራብ ሳዑዲ አረቢያ “ሂጃዝ” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የምትገኘው መካ ከተማ።

ቅዱሷ ከተማ በተራራ የተከበበች ስትኾን በበጋው ወቅት የሙቀት መጠኗ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል፡፡ በሕዝብ ብዛቷ ከሳዑዲ አረቢያ ከተሞች ከሪያድ እና ጅዳ በመቀጠል በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትቀመጣለች፡፡

ከአፍሪካ እና ከሩቅ ምሥራቅ ለሚሄዱ ነጋዴዎች መተላለፊያ መንገድም ኾና አገልግላለች፡፡ በተለይ ከቀይ ባሕር በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷ ለየመን፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ኢራን እና ለምሥራቅ አፍሪካ በተለይም ደግሞ ለኢትዮጵያ ያላት ስትራቴጅካዊ አቀማመጥ የንግድ ማዕከል እንድትኾንም አድርጓታል። ቅመማቅመም፣ መድኃኒት፣ ጨርቃጨርቅ፣ እህል፣ ሽቶ፣ ወርቅ፣ ብር እና ሀር የመሳሰሉ የሸቀጦች ልውውጥም ይካሔድባት እንደነበር ይነገራል፡፡

የሰው ልጆች አሏህን እንዲያመልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በመላዕክቶች አማካይነት መስጅድ የተሠራባት ቦታ ናት፤ አደም ሰባት ጊዜ ተመላልሰው የጎበኟት ቅድስት ስፍራም እንደኾነች ይነገራል፡፡ ነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ከአሏህ ውጭ የሚመለክ የእውነት አምላክ እንደሌለ በሚያስተምሩበት ጊዜ ሕዝቡ በማመጹ አሏህ ዓለምን በጎርፍ ሲቀጣ ከጥፋት የተረፈች ቅዱስ ቦታ እንደኾነች ይነገራል።

ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ኢስማኤልን እና ባለቤታቸውን ይዘው ወደ መካ እንዲጓዙ በአሏህ የታዘዙባት እና ነብዩ ኢብራሂምም የአሏህን ትእዛዝ ተቀብለው ሚስታቸውን እና ልጃቸውን በምድረ በዳዋ ምድር ያኖሩባት ስፍራ ናት፤ ቅዱሷ ከተማ መካ። በሙሳ፣ በኢሳ እና በሌሎች ነብያቶችም የተጎበኘች ቅዱስ ቦታ ተደርጋ ትወሰዳለች።

ከዚህ በፊት ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፣ መካ የተቀደሰ የአሏህ ቤት ያለባት ትልቋ ከተማ ናት፡፡ አሏህ ለመጀመሪያ ጊዜ የአምልኮ ቦታ ያሠሩባት እና ነብዩ ኢብራሂም ካባን ገንብተው ሲጨርሱ ሰዎች በቻሉት ሁሉ ወደዚህ ሥፍራ እንዲመጡ ጥሪ እንዲያደርጉ እና ቤቱ እንዲጎበኝ ያዘዙበት ቦታ ናት።

ሰዎች ተገናኝተው የሚማሩበት እና የሚወያዩበት እንዲትኾን ፈጣሪ የባረካት ከተማ እንደኾነችም ነው የገለጹት ፕሮፌሰር አደም ካሚል፡፡ መካ ላይ የሚደረግ አንድ ሶላት በ100 ሺህ እንደሚታሰብ ተመራማሪው ገልጸዋል።

በዚህ ቅዱስ ስፍራ ምንም አይነት ሐጢአት መሥራት የተከለከለ ነው፡፡ ምን አልባትም በዚህ ቦታ ኾኖ ሀጢያት የሠራ ሰው ከሌላው ጊዜ በተለየ ቅጣቱ በእጥፍ ይጨምራል፡፡
በመካ ተገኝቶ ስግደት ማድረግ በሌሎች ስፍራዎች ከመስገድ በ100 ሺህ እጥፍ ስለሚበልጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ከአራቱም የዓለም ማእዘናት ወደ ቅዱሷ ከተማ ይጎርፋሉ። በየዓመቱም ሙስሊሞች ሀጅ እና ዑምራ ለማድረግ ወደ መካ ያቀናሉ።

መካ ትላልቅ ህንጻዎች እና ትላልቅ መስጅድ ያሉባት ከተማም ናት፡፡ በእጅ የተሠሩ ጡቦች እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች መገኛ በመኾኗ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝበ ሙስሊም እንደሚጎበኟትም መረጃዎች ያሳያሉ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አንድነት የሚጸናበት፤ ለአንድ ፈጣሪ የሚሰገድበት”
Next article“አንድነት የሚጸናበት፤ ለአንድ ፈጣሪ የሚሰገድበት”