
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኅላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ የተመራ ልዑክ ሩሲያ ቪላዲቮስቶክ ገብቷል።
የልዑክ ቡድን ከሰኔ 9 እስከ 12/2016 ዓ.ም በሚካሄደው እና ዎርልድ ማጆሪቲ ፎር መልቲፖላር ኦርደር በሚል መሪ ቃል በሩሲያ ቪላዲቮስቶክ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ነው።
ከፎረሙ ጎን ለጎንም አቶ አደም ፋራህ ከሩሲያ ዩናይትድ ፓርቲ ምክትል የጽሕፈት ቤት ኅላፊ ክሊኖቭ አንድሬ ጋር ተወያይተዋል። አቶ አደም በውይይታቸው ላይ በኢትዮጵያ እና በሩሲያን መካከል ያለውን ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት ያነሱ ሲኾን ኢትዮጵያ በተለያዩ አጋጣሚዎች ችግሮች ሲገጥሟት ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጎን በመኾን ላሳየችው ድጋፍ እና ወዳጅነት ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መኾን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ትልቅ ምዕራፍ መኾኑን ያነሱት አቶ አደም ኢትዮጵያ ብሪክስን እንድትቀላቀል ባደረገችው ጥረትም ሩሲያ ላደረገችው ድጋፍ የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲን እና መንግሥቱን አመስግነዋል።
ቀደም ሲል በሁለቱ ሀገራት የነበሩ የመንግሥት ለመንግሥትም ኾነ የፓርቲ ለፓርቲ ትብብሮች የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንደሚደረግም አቶ አደም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገበች ያለች ሀገር እንደመኾኗም የሩሲያ ባለሃብቶች በመምጣት በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩም ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ቡና፣ አበባ፣ ሰሊጥ ጥራጥሬ እና ሌሎች የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች በቀጥታ ወደ ሩሲያ ገበያ ለመላክ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸውላቸዋል።
የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም የሩሲያ ባለሃብቶች እና የንግዱ ማኀበረሰብ አባላት ኢትዮጵያን እንዲጎበኙም ግብዣ አድርገውላቸዋል።
የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ምክትል የጽሕፈት ቤት ኀላፊ ክሊኖቭ አንድሬ በበኩላቸው በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር የፓርቲያቸው ፍላጎት እንደኾነ ገልጸዋል።
ሩሲያ እና ኢትዮጵያ በሁሉም ጊዜ የማይለዋወጥ እና የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው ይሄንንም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሠሩ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ አዲስ የብሪክስ አባል ሀገር ኾና በመቀላቀሏም እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉት ምክትል የጽሕፈት ቤት ኅላፊው በቀጣይ ዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በተለያዩ መስኮች ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ በፎረሙ ላይ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ በብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኅላፊ አዲሱ አረጋ፣ በብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኅላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር) እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!