
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ትህትና እና መታዘዝ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው እሴቶች ናቸው። በእነዚህ እና ሌሎች እሴቶች የሚገኘው ሃይማኖታዊ እና ሥነ ልቦናዊ በረከት ትልቅ ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ ለአሏህ መታዘዝ ቁልፍ ነገር መኾኑን በእስልምና ሃይማኖት የዲን ተማሪ እና መንፈሳዊ መጽሐፍ ደራሲ ወጣት ሀሊድ ኑርሁሴን ይናገራል። ለአሏህ በመታዘዝ ውስጥ የምናገኘው በረከት በልጅ ልጃችን ለአሏህ እና ለወላጆች የሚታዘዙ ልጆችን ይፈጥርልናል ይላል።
ከመታዘዝ ጋር በተያያዘ መነሻው ወደ ነቢዩ ኢብራሂም እና ወደ ልጃቸው ኢስማኤል የሚወስደን ታሪክ በየዓመቱ ለሚከበረው የዓረፉ በዓል ምክንያት ነው።
ነብዩ ኢብራሂም ሚስታቸው ሳራ ስለማትወልድ ልጅ አልነበራቸውም። ልጅ ሳይኖራቸው ጉልምስናን አልፈው በእርጅና ዘመናቸውም ብቻቸውን ነበር የሚኖሩት። ሳራ ልጅ እንዲኖራቸው ይፈልጉ ስለነበር ኢብራሂምን ከአጋራቸው ከሀጂር እንዲወልድ ትለምነው ነበር። እሱ ግን ይህ መልካም አይደለም አንቺም ቢኾን እየቆየ ቅናት ይሰማሻል አሏት። እርሷ ግን እሺ በጄ እንዲሏት አሳመነቻቸው።
አጋራቸው ሀጂር ፀነስች ወንድ ልጅም ወለደች ሰሙን ኢስማኤል አሉት ። ኢስማኤል የሚለው የሰሙ ምንጭ ኢሽማኤል ከሚል የአብራይስጥ ቃል የመጣ ሲኾን ኢሽማ ማለት ይሰማል ማለት ነው። ኤል ማለት ደግሞ ፈጣሪ ማለት ነው። በሙሉ ትርጓሜው ፈጣሪ ጸሎቴን ስማኝ ማለት ነው።
አንድ ቀን ኢብራሂም ሀጂርን እና ልጃቸው ኢስማኤልን ይዘው ወደ በርሃ ሽኝተዋቸው ተመለሱ። ሀጂር በዚያ በርሃ ልጇን ይዛ ጉዞዋን ቀጠለች የውኃ ጥሙ ግን እጅግ ከበዳት አቃታት። ከአንድ አለት ሥር ተቀመጡ ልጇ በእግሩ መሬቱን እየመታ ሲያለቅስ በእግሩ ከሚመታው አለት ሥር ውኃ ፈለቀ። ደስ አላቸው ጠጡ ረኩም። መንገደኞችም ውኃ እንዲያጠጡዋቸው ጠይቀው በምትኩ ቴምር እየሰጧቸው ያልፉ ነበር።
ኢብራሂም በህልሙ ልጅህን እረድ የሚል መልዕክት ከአሏህ ደረሰው እውነት ለመኾኑ ሶላት እያደረገ ይጠብቅ ነበር። ለሦስት ጊዜያት ይህን ህልም ካየ በኋላ በርሃውን አቋርጦ ልጁ ወዳለበት ተመልሶ ሄደ።
ኢብራሂም የፈጣሪው ትዕዛዝ በመኾኑ በልጁ ላይ ቢላዋ ለማንሳትም ቢኾን አላመነታም ልጁን መስዋዕት ለማድረግ ልቡ ፈቀደ። ለኢስማኤል ከፈጣሪው የተሰጠውን ትዕዛዝ ሲነግረው አባቴ ኾይ የፈለከውን አድርግ እኔ ከታዛዦችህ አንዱ ሆኘ ታገኘኛለህ በማለት ለአባቱ በትህትና ራሱን መስዋዕት አድርጎ አቀረበ።
የኢስማኤል ለአባቱ መታዘዝ ኢብራሂም ለፈጣሪው ያሳየው የታዛዥነት ውጤት ነው በማለት ወጣቱ ጸሐፊ ሀሊድ ኑርሁሴን አስረድቷል።
አባት የፈጣሪውን ቃል በማክበር የኢስማኤልን እጅ ለኋሊት አሰረ ቢላዋውን በልጁ አንገት ላይ ለማድረግ እጆቹ ወደፊት አመሩ ልጅ በትህትና ራሱን የተወደደ መስዋዕት አድርጎ ቀረበ። ትህትና እና መታዘዝ ነፍስ ዘርተው አካል ፈጥረው የተገለጡበት ኹነት ተፈጠረ።
የአባትን ታዛዥነት የልጅን ትህትና በጽናት ለፈጣሪያቸው በማሳየታቸው ለመስዋዕት የሚኾን ሙክት ከሰማይ ወረደ።
በቅዱስ ቁርአን የአሏህ ወዳጅ ተብለው የሚጠሩት ነቢዩ ኢብራሂም በልጃቸው ፈንታ ከሰማይ የወረደላቸውን መስዋዕት አቀረቡ።
የዓረፋ በዓል ሲከበር የእርድ ሥነ ሥርዓት የሚፈፀመውም ይህን በማሰብ ነው። በእርድ የሚከበረው በዓል በዚህ ብቻ የሚከበር ሳይኾን ለአሏህ መታዘዝ ያለውን መንፈሳዊ በረከት የምናስታውስበት ነው፡፡
የነቢዩ አብራሂም እና የኢስማኤል ታዛዥነት በዚህ ብቻ የሚታወስ አይደለም። አሏህ ኢብራሂም ከልጁ ጋር በመኾን በትውልድ የሚመለክበትን ካባ ሥራ የሚል ትዕዛዝ ተሰጠው።
ከዛም አስፈላጊውን ቁሳቁስ አሠባሥበው ካባን በመካ አሠሩ። አሁን ይህ ቅዱስ ስፍራ ብዙ ቱሪስቶች እና አማኞች በየዓመቱ የሚጎበኙት ድንቅ የጽድቅ ምድር ተደርጎ በአማኞች ይታመንበታል።
የአሁኑ ትውልድ ከምዕራባውያን የባሕል ጫና ተላቅቆ ከነቢዩ ኢብራሂም እና ኢስማኤል ታዛዥነት እና ትህትናን እንዲሁም ሃይማኖታዊ እሴቱን መተግበር እና መላበስ አለበት ያለው ሀሊድ ኑርሁሴን የሃይማኖት ተቋማት እና ትምህርት ቤቶችም ይህን እሴት የሚያጎለብት ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ተናግሯል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
