“በዓሉ የመልዕክተኛዉን ፈለግ የምንከተልበት ሰብዓዊነት የሚደምቅበት ዕለት ነዉ” የጎንደር ከተማ እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሀጅ አንዋር ቃሲም

13

ጎንደር: ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺህ 445ኛዉ የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል በጎንደር ከተማ በሶላት እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ሥረዓቶች ተከብሮ ዉሏል።
በበዓሉ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸዉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የሃይማኖቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።

በበዓሉ ለተገኙ ምዕመናን ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሀጅ አንዋር ቃሲም ነብዩ ኢብራሂም በአሏህ ትዕዛዝ የበኩር ልጃቸዉን እስማኤልን ለመሥዋዕት እንዲያቀርቡ ታዘዉ የአሏህን ትዕዛዝ ካለመወላወል ለመፈጸም ፈቃደኛ የኾኑበት እና የተዛዥነትን ጥግ ያስተማሩበት ነዉ ብለዋል። ሕዝበ ሙስሊሙም ከዚህ የደግነት እና የታዛዥነት ጥግ ሊማር እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

“በዓሉ የመልዕክተኛዉን ፈለግ የምንከተልበት ሰብዓዊነት የሚደምቅበት ዕለት ነዉ” ብለዋል ሀጅ አንዋር ቃሲም። አሏህ ሀገራችንን እንዲያረጋጋት ዱዓ የምናደርግበት፣ ለሀገራቸዉ ሕይወታቸውን እየሰዉ ላሉ ወገኖች ምሥጋና የምናቀርብበትም ነው ብለዋል ።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ ኢትዮጵያ የበርካታ ሃይማኖቶች እና ባሕሎች ባለቤት ናት፤ እነዚህ ባሕል እና እሴቶቻችን የሀገራችን ሕዝብ ለዘመናት የተገመደበት የአብሮነት ገመድ፣ የእኛነታችን መገለጫዎች ስለኾኑ ትውልዱ ዐውቆ ሊያስቀጥላቸዉ ይገባል ብለዋል።

አቶ ባዩህ አቡሃይ አክለውም የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓልን ስናከብር በሃይማኖት አስተምህሮ መሰረት የተቸገሩ ወገኖችን ማዕድ እያጋራን፣ ያለንን እያካፈለን፣ ደስታ ለሌሎች እየዘራን ሊኾን እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዓሉን ሲያከብሩ ያገኘናቸዉ ምዕመናን በበኩላቸዉ ዓረፋ የመሥዋዕት ቀን መታሰቢያ እንደመኾኑ በመረዳዳት፣ በአብሮነት እና የተቸገሩትን በመደገፍ እያከበሩት መኾኑን ነግረዉናል።

ዘጋቢ:- አዲስ አለማየሁ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዒድ ሰላት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ መጠናቀቁን የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡
Next articleበትህትና እና በመታዘዝ የቀረበ መስዋዕት፡፡