በዒድ ቀን መልካም የሚሠራበት፣ የሚተዛዘኑበት እና የሚረዳዱበት በዓል ነው።

17

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺህ 445ኛው የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል በባሕር ዳር ከተማ ባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ተከብሯል። በበዓሉ የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ጁሃር ሙሀመድ፣ የምክር ቤቱ ዋና ሰብሳቢ ረዳት ፕሮፌሰር ምርታቸው ጧሂር፣ የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፣ የከተማዋ አመራሮች እንዲሁም የባሕር ዳር ከተማ እና አካባቢው ሙስሊሞች ተገኝተዋል።

በዓሉ በስግደት፣ በጸሎት እና በሃይማኖታዊ ትምህርት ተከብሯል። የበዓሉ ተካፋይ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት ካሊድ ኑርሁሴን “ቀኑ በአሏህ ዘንድ እጅግ የተከበረ ነው። ይህ በዓል ነቢዩ ኢብራሂም የፈጣሪያቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው ልጃቸውን እስማኤልን ሊያርዱበት የነበረው እና አሏህም ታዛዥነታቸውን አይቶ በምትኩ የሚታረድ በግ የላከበት መታሰቢያ ነው” ብሏል።

የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል መታዘዝ እና እዝነት የሚታይበት በዓል መኾኑን ገልጿል። በዚህ በዓልም የሚፈጸመውን እርድ ከሦስት ተካፍሎ ለችግረኞች የሚረዳበት ነውም ብሏል። በእስላማዊ አስተምህሮው መሰረትም ሕዝበ ሙስሊሙ ችግረኞችን በመርዳት በዓሉን እንዲያከብር አሳስቧል።

በባሕር ዳር ሰላም በር መስጂድ የዳእዋ ዘርፍ ኀላፊ እና የጁምዓ እና የኢድ ኢማም ሼህ መሐመድ አደም (ዶ.ር) ዒድ አል አድሃ የረፋድ ደስታ ማለት ሲኾን በዕለቱ ሶላት ከተሰገደ በኋላ እርድ ፈጽሞ ለሌላው በማካፈል የሚደሰቱበት በዓል መኾኑን ጠቅሰዋል።

መሐመድ አደም (ዶ.ር) አክለውም በዒድ ቀን መልካም የሚሠራበት፣ የሚተዛዘኑበት እና የሚረዳዱበት በዓል መኾኑን ገልጸዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ ረዳት ፕሮፌሰር ምርታቸው ጧሂር በዓሉ ለሙስሊሞች ታላቅ ሃይማኖታዊ ዳራ ያለው መኾኑን ገልጸዋል። ”ነቢዩ ኢብራሂም ለፈጣሪያቸው ታዛዥነትን ያሳዩበት እና ልጃቸው እስማኤልም ለፈጣሪያቸው እና ለአባታቸው ያሳዩት መታዘዝ ለሰው ዘር በሙሉ በተለይም ለወጣቶች ትምህርት የሚኾን ነው” ብለዋል።

በዓሉ የእርድ በዓል በመኾኑም እምነታችን በሚያዝዘው መሰረት ከሦስት አንዱን ለሚስኪኖች በማካፈል ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ተደስቶ እንዲውል አደራ ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሰላም ሀገር እና ለስደተኞች መጠለያ እንደነበረች አስታውሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየውን የሰላም እጦት አሏህ እንዲያስወግድልን ሁሉም ሙስሊም በዱዓ እንዲጠናከር አሳስበዋል።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጸሐፊ ኡስታዝ አብዱራህማን ሱልጣን ”ሰላም የሁሉም መሰረት ነው። እስልምና ሰላም ነው። ሀገራችንን ሰላም እንዲያደርግልን ሁላችንም ዱዓ እናድርግ” ብለዋል።

ሀገራችን ውስጥ በስደት የሚገኙ ምስኪኖችን በተከበረው ዒድ አል አደሃ በሰደቃ እንድናስባቸው ይሁን ሲሉም አሳስበዋል። ”በዓላችን የሰላም፣ የአንድነት፣ የመተባበር እና የእዝነት እንዲያደርግልን እንዲኹም አሏህ ምህረቱን እንዲለግሰን ሁላችንም ዱዓ እናድርግ” ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰይጣን ከዓረፋ ቀን የበለጠ ተዋርዶ የሚታይበት ቀን የለም” ዶክተር ሼህ ሙሐመድ ከማል
Next articleየዒድ ሰላት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ መጠናቀቁን የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡