
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሼህ ሙሐመድ ከማል (ዶ.ር) እንዳሉት ዒድ ማለት የዓረፋ ሰዎች ምሕረት ተደርጎላቸው እናንተንም ምሬአለሁ እናንተ ማሩ ያላችሁኝን ሰዎችም ምሬአለው ተብለው በፍቃድ ወደ ሙስደሊፋ የሄዱበት ቀን ነው፡፡
ዛሬ ዒዳቸው ነው፣ ሚና አድረው፣ ጀመረተል አቀባ ላይ ጠጠር ወርውረው፣ ተላጭተው እና ለእርድ የተዘጋጀውን አርደው ዒዳቸውን ይሰግዳሉ። እኛም እንደነሱ ዒዳችንን ሰግደንና ጹመን የሁለት ዓመት ወንጀል ተምረን፤ አሏህ ከሚምራቸው ተርታ እንኾናለን ብለዋል፡፡
ዶክተር ሼህ ሙሐመድ የዒዱን አመጣጥ ሲናገሩ ለሙስሊሞች ሦስት ዒድ አላቸው ነው ያሉት። ሁለቱ በየዓመቱ የሚመጡ ናቸው፡፡ በየቀኑ አምስት ሶላት እየተሰገደ ሰባት ቀን ሲሞላ ሰባተኛውን ቀን ጁምዓን ነብያችን ለእኛ ዒድ አድርገውልናል ነው ያሉት፡፡
ሁለተኛው ዒድ ደግሞ ሙስሊሞች ረመዷንን ከጨረሱ በኋላ ተሠብሥበው አሏህን የሚያመሠግኑበት ሽልማታቸውን የሚቀበሉበትን አሏህ ዒድ አደረገላቸው ነብዩም ሲናገሩ ይህን ሕዝበ ሙስሊሙ መሥራቱን አስረድተዋል፡፡ ዛሬ የሚከበረው ዒድ አል አድሃ ደግሞ ሦስተኛው ዒድ ነው።
ዶክተር ሼህ ሙሐመድ ከማል ዓረፋ እና ዒድ አል አድሃ እንደሚለያዩ መታወቅ እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት፡፡ ዓረፋ የሚባለው ሙስሊም በሕይዎቱ አንድ ጊዜ ሂዶ አርዶ ዓረፋ ላይ (ጀበሉ አራህማ) ዙሪያ በመሄድ የተለያዩ ሂደቶች ያሉትን የሃጂን ግዴታ ሲፈጽም ይህም መካ ዓረፋ ይባላል ብለዋል።
ዛሬ የሚከበረው ዒድ ግን ዒድ አል አድሃ ይባላል፤ ይህም ሰግደው ተመልሰው በረፋድ አርደው የሚደሰቱበት ቀን ነው ብለዋል፡፡ ሰይጣን ከዓረፋ ቀን የበለጠ ተዋርዶ የሚታይበት ቀን እንደሌለም ነው ዶክተር ሼህ ማሕመድ ከማል (ዶ.ር) ያብራሩት፡፡
ሙስደሊፋ ላይ ነብዩ ሰው ሁሉ ተኝቶ ለሰው ልጅ ዱዓ ሲያደርጉ አሏህ ዱዓቸውን (ጸሎታቸውን) ሲቀበላቸው ነብዩ በጣም መሳቃቸውን ተናግረዋል። ነብዩ ለምን ሳቁ ተብለው ሲጠየቁ አሏህ እኔን ዱዓዬን ሲቀበለኝ እና ሕዝቦቼን ሲምርልኝ ሰይጣን ተንበርኮ ራሱ ላይ አፈር እየደፋ አየሁት በማለት እንደተናገሩ ነው ያብራሩት፡፡ ይህ ቀን አሏህ ለአማኞች አጅር (ምንዳ) የሚሰጥበት ቀን በመኾኑ አሏህን ማመስገን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከዒድ ሶላት በኃላ እርድ እንደሚፈጸም ተናግረዋል፡፡ ዶክተር ሼህ ሙሐመድ ከማል እንደተናገሩት ከሶላት በፊት ያረደ ለቤተሰቡ ስጋ ሰጠ እንጂ በእስልምና አስተምህሮት እርድ የሚፈጸምበትን አጅር (ምንዳ) እንደማያገኝ ነብዩ ስለመናገራቸው ነው የተናገሩት፡፡
የዛሬውን የዒድ ቀን ሙስሊሞች በተስቢህ፣ በተህሊል፣ በተህሚድ እና ዝምድና በመቀጠል ማክበር እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
