“ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓልን ሲያከብር የቆየውን የመረዳዳት እና የአብሮነት እሴቱን የበለጠ በማጠናከር ሊኾን ይገባል” የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸሪዓ ፍርድ ቤት ዳኛ ሼህ ወለላው ሰይድ

24

ደብረ ማርቆስ፡ ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺህ 445ኛው የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በዒድ ሶላት እና በሌሎች ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በደብረ ማርቆስ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡

በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልክት ያስተላለፉት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸሪዓ ፍርድ ቤት ዳኛ ሼህ ወለላው ሰይድ የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው እስማኤልን በአሏህ ትእዛዝ ለመስዋእት ሲያዘጋጁ በምትኩ በግ መቅረቡን የሚያስታውስ በመሆኑ የመስዋዕት በዓል ተብሎም ይከበራል ብለዋል።

ሼህ ወለላው ሰይድ በመልዕክታቸው “ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓልን ሲያከብር የቆየውን የመረዳዳት እና የአብሮነት እሴቱን የበለጠ በማጠናከር ሊኾን ይገባል” ብለዋል። በበዓሉ የተቸገሩ ወገኖችን ማብላት እና ማጠጣት እንዲኹም የታረዙትን ማልበስ እና መንከባከብ እምደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ሀገራችን አሁን ካለችበት ችግር እንድትወጣ ሕዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች ወንድሞቹ እና እህቶቹ ጋር በመኾን ለሰላም ተግቶ መሥራት እና ዱዓ ማድረግ እንደሚገባውም ሼህ ወለላው ሰይድ አሳስበዋል፡፡

በበዓሉ ላይ ያገኘናቸው ሱሌማን ደሴ እና እንድሪስ አደም የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል አንድነት እና መተባበር የሚገለጥበት፤ ምስኪኖች እና የተቸገሩ ወገኖች የሚጎበኙበት በዓል መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ሰላም ከሌለ እንደዚህ ተሰባስቦ በዓል ማክበር የማይቻል በመኾኑ በዓሉን ለሀገር ሰላም በመጸለይ፣ ለሰላም ዘብ በመቆም እና በመደጋገፍ እንደሚያሳልፉም አስተያየታቸውን ሰጠዋል፡፡

በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች በደብረ ማርቆስ ከተማ የተከበረው የዒድ አል አድሃ ዓረፋ በሰላም ተጠናቋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢንሻአሏህ ይህ ብዙ በረከቶችን ያመጣል” ቱርካዊት የሀጂ ተጓዥ
Next article1 ሺህ 445ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓል በኮምቦልቻ ከተማ ተከብሯል።