
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በየዓመቱ በእስልምና አቆጣጠር በመጨረሻው ወር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች የሀጂ ተግባር ለመፈጸም ወደ ሳዑዲ አረቢያዋ ቅዱስ ከተማ መካ ይሄዳሉ።
ሀጂ ከአምስቱ የእስልምና መሠረቶች አንዱ ሲኾን ሁሉም ሙስሊም የአካል እና የገንዘብ አቅማቸው ከፈቀደ በሕይዎታቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል።
ለብዙ ምዕተ ዓመታት ሴቶች ከወንድ የቤተሰባቸው አባል ጋር በጋራ እንዲሄዱ የሚያስገድድ ገደብ ነበር። ይህ ገደብም እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2021 የሳዑዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን መንግሥቱን ለማዘመን በወሰዱት እርምጃ ሊነሳ ችሏል።
ይህ ውሳኔ የወንድ ቤተሰብ ለሌላቸው ወይም ብቻቸውን የሀጂ ጉዞ ማድረግ ለሚፈልጉ ሴቶች ትልቅ እፎይታ ፈጥሮአል። የ41 ዓመቷ ፋህሪ ከእነዚህ ሴቶች አንዷ ናቸው።
ፋህሪ አሁን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ቁጥር ካለው የሀጂ ተጓዥ ጋር መካ ነው የሚገኙት። ፋህሪ የነብዩ ኢብራሂምን ባለቤት ሃጀርን ታሪክ እንደተጋሩም ያስባሉ።
“ከዚህ ቦታ ላይ የሃጀርን ሚና እየተወጣሁ ነው። እሳቸው የፈጣሪያቸውን ትእዛዝ በፍቅር ተቀብለው ቤታቸውን እና ዘመዶቻቸውን በመተው ያለ ማንም ጠባቂ ብቻቸውን ከዚህ ቦታ ተገኝተው ነበር” ሲሉ ስሜታቸውን ለቱርኪየ ቲ አር ቲ ወርልድ ሚዲያ ተናግረዋል።
ፉህሪ ወደ መካ ከባለቤታቸው ጋር ለመምጣት አስበው የነበረ ቢኾንም ባለቤታቸው በግል ጉዳይ ምክንያት አብሮ መምጣት እንዳልቻለ እና ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር አብረው እንዲሄዱ ሃሳብ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።
ፋህሪ የሀጂ ጉዟቸው ለዓለም ያላቸውን አመለካከት እና ሌሎች እይታዎችን የቀየረ ስለመኾኑ ተናግረዋል። “ኢንሻአሏህ (እንደአሏህ ፈቃድ) ይህ ብዙ በረከቶችን ያመጣል” ብለዋል ፋህሪ
ሴቶች ከወንድ ቤተሰቦቻቸው ውጭ የሀጂ ጉዞ እንዳያደርጉ የሚከለክለው ገደብ መነሳቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከወንዶች ጋር መምጣት ለማይችሉ በርካታ ሴቶች ለቅዱሱ የሀጂ ጉዞ በር የከፈተ ነውም ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
