
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጠቢባን የጥበብን ባለቤት ይከተላሉ፤ በእርሱ ጎዳና ይጓዛሉ፣ ሕግጋቱን ያውቃሉ፣ አብዝተው ይጠብቃሉ፣ ያስጠብቃሉ፣ ብልሆች ትዕዛዛትን ያከብራሉ፣ በመታዘዝ ከክብር ላይ ክብር ይጨምራሉ፣ በመታዘዝ አምላካቸውን ያስደስታሉ፣ በመታዘዝ በምድርም በሰማይም ይወደዳሉ፣ በመታዘዝ አርዓያና ምሳሌ ይኾናሉ፣ በመታዘዝ መልካሙን ነገር ያደርጋሉ፣ በመታዘዝ ስማቸውን በሕይወት መዝገብ ላይ ያሳርፋሉ፡፡
ብልኾች እና አማኞች እስከ ሞት ድረስ ይታዘዛሉ፣ አባታቸው ያላቸውን አሜን ብለው ይቀበላሉ፣ አባት የጠየቃቸውን ያለ ምንም ማንገራገር ይፈጽማሉ፣ ይሁን ይደረግ ብለው ቃሉን ይተገብራሉ እንጂ፡፡
ሳይጠራጠሩ መታዘዝ እንደ ምን ያለ ቅንነት ነው? ከዕምነት ሳይጎድሉ መታዘዝ እንደምን ያለ ዕምነት ነው? ልጅን ለመስዋዕት እስከ ማቅረብ ደግ መኾንስ እንደ ምን ያለ ደግነት ነው?
ጠቢባን የፈጣሪያቸውን ቃል ያለ መጠራጠር ይቀበላሉ፣ ተቀብለውም ቃሉን በተግባር ይኖራሉ፣ ሕጉን ሳይሸርፉ ይተገብራሉ፣ ሳይሽሩም ይጠብቃሉ፣ ያስጠብቃሉ፡፡ ከቃሉ ሳያጎድሉ፣ ከቃሉም ሳያልፉ ይኖራሉ፡፡
ሙስሊሞች በፈጣሪ ዘንድ የሚወደዱትን፣ የተመሰከረላቸውን፣ ፈጣሪን የሚፈሩ ተብለው በቁርዓን የተጻፈላቸውን ነብዩ ኢብራሂም በአምላካቸው ትዕዛዝ ልጃቸውን ለመስዋዕትነት ያቀረቡበትን፣ ልጃቸው እስማኤልም የአባቱን ትዕዛዝ የተቀበለበትን በዓል በታላቅ ድምቀት ያከብሩታል፡፡ ኢብራሂም የፈጣሪያቸውን ትዕዛዝ ተቀበሉ፣ እርሳቸውም ልጃቸውን አዘዙ፣ ልጃቸውም የእርሳቸውን ትዕዛዝ ተቀበለ፡፡ ይህችም ትዕዛዝ የተወደደች፣ የተመረጠች፣ የተከበረችም ናት፡፡
ስለ ምን ቢሉ በመታዘዝ ክብር ተገኝቶባታል፤ በመታዘዝ ፈጣሪ ደስ ተሰኝቶባታልና፡፡ ይህች ቀን በሙስሊሞች ዘንድ ዒድ አል አደሃ ዓረፋ እየተባለች ትከበራለች፡፡
በዚህች ቀን መስዋዕት ይታሰብባታል፤ መታዘዝም ከፍ ብሎ ይነገርባታል፡፡ ለዚያውም እስከ ሞት የሚደርስ መታዘዝ፣ መታዘዝ ከሞት የበለጠበት ቅንነት ይታሰባል፡፡
ኢብራሂም ልጄን ለመስዋዕትነት አላቀርብም አላሉም፣ በፈጣሪያቸው ቃል አልተጠራጠሩም፣ የተባሉትን በቅን ልቡና ተቀብለው ታዘዙ እንጂ፤ ልጃቸውም መስዋዕት አልኾንም አላለም፤ የአባቱን ትዕዛዝ ተቀበለ እንጂ፡፡ ይህችም ሳይጠራጠሩ ለፈጣሪ መታዘዝ ዛሬም አብዝታ ታስፈልጋለች፡፡
በዓረፋ በዓል መስዋዕት፣ አንድነት፣ መታዘዝ እና ሌሎች መልካም ነገሮች ይታሰባሉ፡፡ በዚህች የተመረጠች በዓል ወላጆችም ልጆችም በፍቅር ያሳልፋሉ፣ ትሕትናንም ያደርጋሉ፡፡ በተለይም ወጣቶች መታዘዝን ገንዘባቸው ያደርጉ ዘንድ ይፈለጋል፤ ይጠበቃልም፡፡
የእስልምና ሃይማኖት ተከታዩ ወጣት አሕመድ ወንዴ ከአሚኮ ጋር በነበረው ቆይታ እንዳለው በዓረፋ በዓል ለጌታ የሚደረግን ታዛዥነት፣ የአባት እና የልጅ መስተጋብር፣ ልጅ ለምን ሳይል የአባትን ቃል መቀበል የሚታሰብበት ነው ብሏል፡፡ በዚህች ቀን ትክክለኛ አማኝነት፣ ፍጹም መታዘዝ ጎልቶ ይታያል፡፡ ትዕዛዝን መቀበል ታላቅ ክብርን ያሰጣል፤ ትዕዛዝን ማክበር በፈጣሪ ዘንድ ያስከብራል፤ ልጆች ወላጆቻቸውን፣ ታላላቅ ሰዎችን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ፈጣሪያቸውን ሊታዘዙ ግድ ይላቸዋል ነው የሚለው፡፡
መታዘዝ ሲኖር መከባበር አለ፣ መከባበር ሲኖር ፍቅር ይኖራል፤ ፍቅር ሲኖርም ሰላም አለ፡፡ ከራስ በላይ ለሌሎች ማሰብ፣ ለሌሎች መኖር፣ ማክበር በዓረፋ በዓል ቀን ሊደረጉ የሚገባቸው ናቸው፡፡ በእርግጥ መልካም ነገርን በበዓላት ቀን ብቻ ሳይኾን በየትኛውም ጊዜ ማድረግ ታላቅነት ነው ይላል አሕመድ፡፡ የዓረፋ በዓል አብሮ መኖርን፣ በሌሎች ደስታ መደሰትን፣ ከራስ ቀንሶ ለሌሎች መስጠትን የሚያስተምር እና የሚያዝዝ ነው፡፡
አሕመድ እንደሚለው ደካሞችን በበዓላት ብቻ ሳይኾን በየትኛውም ጊዜ ማገዝ፣ ለታላላቆች መታዘዝ የተገባ ነው፡፡ ትክክለኛ አማኝ ማለት ለራሱ እንዲኾንለት የሚፈልገውን ለሌሎች ለማድረግ የሚወድ ነው፣ ይሄን ያላደረገ ትክክለኛ አማኝ አይደለም፤ ጀነት መግባትን የሚፈልግ፣ ጀነት የሚያስገባውን በምድር ላይ ማድረግ አለበት፤ ኢብራሂም ያደረጉት ይሄን ነው፣ ልጃቸው እስማኤልም እንዲህ ነው ያደረጉትና ይላል፡፡ ጀነት በምኞት ብቻ አትገኝም፡፡ ጀነት የምትገኘው ትዕዛዝን በማክበር ትክክለኛ አማኝ በመኾን ነውና፡፡
በኢትዮጵያ ታናሽ ታላቅን ማክበር፣ ለታላቅ መታዘዝ፣ ታላቅ የሚለውን መስማት፣ ሰምቶ መተግበር ነበር፤ አሁን ያ ነገር ቀንሷል፤ እነዚያ የተወደዱ የኢትዮጵያውያን መገለጫዎች እየተሸረሸሩ ነው፤ ግድ የለም ወደ ማንነታችን እንመለስ ይላል አሕመድ፡፡ እናት አባትን ማክበርን፣ ለእነርሱ መታዘዝን አጥብቆ መያዝ ይገባል፤ ለልጆች ከፊደል አስቀድሞ ምግባርን ማስተማርን መልመድ፣ ማጠንከር ይገባልም ይላል፡፡
ትዕዛዝን ማክበር፣ በጎነትን ማድረግ፣ ሃይማኖት ምን ይላል የሚለውን መመርመር ወደ አንድነት ወደ ፍቅር ያመጣል፤ ለምን ቢባል ሁሉም ሃይማኖት መጥፎ ነገርን ይከለክላል፣ መልካም ነገርንም እንድናደርግ ያዝዛልና ነው የሚለው፡፡ የሃይማኖት አባቶችን እንስማቸው፣ ሰከን ብለን እናስብ ይላል፡፡
ከኢብራሂም፣ ከልጃቸውም ከእስማኤል አስቀድሞ ነገር ለዕምነት ማደርን፣ ማመንን፣ ሳይጠራጠሩ መታዘዝን፣ በምግባር መኖርን፣ ለሃይማኖት መሰጠትን መማር አለብን ነው ያለው፡፡ ጀነትን ለማግኘት ካለምን ታዛዥነትን ማሰብ አለብን፣ ስሜትን ሳይኾን ዕምነትን እንከተል፤ ለእውነት እንኑር፣ አማኝ ስንኾን እውነትን እንቀበላለን፣ ለእውነትም እንኖራለን፣ አባት እና እናትን ካከበርን፣ ሃይማኖትን ከጠበቅን በሰማይም በምድርም እንከበራለን ነው ያለው፡፡
ሌላኛው ወጣት ካሊድ ኑርሴን ስለ ዓረፋ ሲናገር አሏህ በተወደዱና በተከበሩ ወራት ውስጥ ነፍሶቻችሁን አትበድሉ ይላል፤ ከእነዚህ ከተወደዱ ወራት አንደኛው የዓረፋ በዓል የሚከበርበት ዙል ሂጃ የሚባለው ወር ነው ብሏል፡፡ ዒድ አል አደሃ እና ዒድ አል ፈጥር ሙስሊሞች ነፍሳቸውን የሚያስደስቱባቸው፣ ታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓትን የሚያደርጉባቸው ናቸው፡፡
ኢብራሂም ልጅህን ሰዋ ተብለው ነበር፣ እሳቸውም ልጃቸውን ልሰዋህ ነው አሉት፤ ልጃቸው እስማኤልም አሏህ አዝዞሃልና የፈለከውን፣ የወደድከውን አድርግ፣ እኔንም ከታጋሾቹ ኾኔ ታገኘኛለህ አለ፣ ዓረፋም የታዛዥነት በዓል ነው፤ አንተ ለፈጣሪ ስትታዘዝ፣ የአንተ ልጅም ለአንተ ይታዘዝሃል፤ ኢብራሂም ለፈጣሪያቸው ታዘዙ፣ ልጃቸው እስማኤልም ለእርሳቸው ታዘዘ፣ ወጣቶች ከፈጣሪያቸው ቀጥለው ወላጆቻቸውን መታዘዝ አለባቸው፣ ይሄንም ያዘዘው አሏህ ነው፤ ለወላጆቻችሁ መልካም ልጅ ሁኑ፤ ወላጆቻችሁን በመጥፎ ቃል እንኳን እንዳትጠሩ ይላል ነው የሚለው፡፡
ሀገር ሰላም ትኾን ዘንድ፣ ፍቅርም እንዲኖር አንድ መኾን ነው፣ አሏህ አንድ ሁኑ፣ አትለያዩ፣ ጠበኞች በነበራችሁ ጊዜ አሏህ በእናንተ ላይ የዋለውን ውለታ አስታውሳችሁ ወደራሳችሁ ተመለሱ፤ ሙስሊሞች በተለያዬ ጎሳ ቢለያዩም ሀጂ የሚሄዱት አንድ ቦታ ነው፣ ሙስሊሞች የተለያየ መልክ ቢኖራቸውም፣ የተለያየ ሃብት ቢኖራቸውም ተመሳሳይ ልብስ ለብሰው ሀጂ ላይ ይቆማሉ፡፡ ሙስሊሞች የተለያዬ አመለካከት ቢኖራቸውም ከቁርዓን የተለየ መለኮታዊ መመሪያ የላቸውም፡፡ ሁሉንም አንድ የሚያደርግ አለ፤ ቅርንጫፎቹን ትተን ወደ ዋናው አንድ ወደ ሚያደርገው እንምጣ ነው ያለው፡፡
አንድነት ሙስሊሞች ለሙስሊሞች ብቻ ሳይኾን ከሌሎች ጋርም አንድነት እንዲኖር ሃይማኖት ያዝዛል፤ አንድ የሚያደርገን ብዙ ነገር አለ፤ አንድ እንሁን ብሏል፡፡ በተወደደችው ወር፣ በወተደደችው ቀን የተወደውን አድርጉ፡፡ በምድርም በሰማይም ትከበሩ ዘንድ ታዛዦች ሁኑ፡፡ ሕግንም ጠብቁ፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
