
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 1ሺህ 445ኛው የዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓል በባሕር ዳር ከተማ እየተከበረ ነው። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የእንኳን አደረሳቹህ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓልን ለማክበር የቻልነው የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለሰላም ከፍተኛ ሥራ በመሥራቱ መኾኑን ገልጸዋል። እስልምና ሰላም መኾኑን ያነሱት ከንቲባው በቀጣይም ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንዳሉት ከዚህ በፊት በከተማ አሥተዳደሩ ለበዓል ማክበሪያ ለተጠየቀው ጥያቄ የቦታ ካሳ ክፍያ ተከፍሏል፡፡ ካርታና ፕላን እንዲሠራም ተወስኗል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከተማ አሥተዳደሩ እንደሚያስረክብም ገልጸዋል።
ሌሎች ጥያቄዎችንም ሕግና ሥርዓት በሚያዘው መሠረት ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መላው ሕዝብ በመደማመጥ ለጋራ ሀገር መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ በከተማ አሥተዳደሩ የክረምት በጎ አድራጎት ሥራ እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
