በአማራ ክልል በልዩ ልዩ ምክንያቶች ለከፋ ችግር ለተጋለጡ ሕጻናት አገልግሎት የሚሰጥ የሕጻናት እንክብካቤ እና ድጋፍ ማዕከል ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።

24

ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በባሕር ዳር ከተማ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ አድርጎ ያስገነባውን የሕጻናት፣ እንክብካቤ እና ድጋፍ ማዕከል ለአገልግሎት ዝግጁ አድርጓል።

ማዕከሉን የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) እና የክልሉ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኅላፊ ብርቱካን ሲሳይ መርቀውታል።
ይህ ዘመናዊ እንደኾነ የተነገረለት የሕጻናት፣ እንክብካቤ እና ድጋፍ ማዕከል በልዩ ልዩ ምክንያቶች ለከፋ ችግር የተጋለጡ ሕጻናትን ተቀብሎ ድጋፍ እና እንክብካቤ ያደርጋል ነው የተባለው።

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) መሥሪያ ቤታቸው ለማዕከሉ የተለያዩ ግብዓቶች ማሟያ አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል። እፎይታ የበጎ አድራጎት ማኅበር በማዕከሉ በመገኘት ለ120 ሕጻናት እና በችግር ላይ ለሚገኙ ለሕጻናቱ ቤተሰቦች 500 ሺህ ብር የሚገመት የአልሚ ምግብ፣ የምግብ ዱቄት እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓልን ሲያከብር በአብሮነት እና በመረዳዳት መንፈስ ሊኾን ይገባል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
Next article“የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓልን ስናከብር የሀገራችንን ክብር እና የሕዝባችንን አንድነት የሚያጠናክር እንዲሆንልን ከልብ እመኛለሁ” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ