የወባ በሽታ ስርጭት የጤና ስጋት እየኾነ በመምጣቱ ከፍተኛ መሪዎች አጀንዳ አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ ተመላከተ።

24

ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የወባ ስርጭት ጫናን በዘላቂነት ለመግታት ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል። የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ባልተጠበቀ ሁኔታ እየጨመረ የመጣው የወባ በሽታ ስርጭት በኅብረተሰቡ ላይ ማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን አስከትሏል ብለዋል።

በኢትዮጵያ 75 ከመቶ የሚኾነው አካባቢ ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ መኾኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ድኤታው የወባ በሽታ ስርጭት ለኅብረተሰባችን የጤና ስጋት እየኾነ መምጣቱን የተደረጉ ጥናቶች ስለሚያመለክቱ በተለይ ከፍተኛ መሪዎች አጀንዳ አድርገው እንዲሠሩ አሳስበዋል። ዶክተር ደረጀ አክለውም እንደ ሀገር በአማራ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ እና ኦሮሚያ ክልሎች ስርጭቱ እየተስፋፋ መኾኑን ተናግረዋል። በተለይ በሰሜን ምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ 222 ወረዳዎች ላይ የወባ በሽታ ስርጭት መጨመሩን ተናግረዋል።

ሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በቅንጅት በመሥራት እንዳለፈቻቸው ያስታወሱት ዶክተር ደረጀ ልክ እንደ ኮቪድ 19 በክላስተር ግብረ ኀይል በማዋቀር ለቀጣይ ስድስት ወራት ባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅቶችን በማቀናጀት ስርጭቱን በእጅጉ ለመቀነስ ጤና ሚኒስቴር ጥብቅ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ክልሉ የጀመራቸውን የጤና ልማት ሥራዎች ማስቀጠል የሚቻለው ማኅበረሰቡ ጤናማ ሲኾን እንደኾነ ጠቁመው አሁን ያለው የወባ ስርጭት ስጋት እንደኾነባቸው አሳውቀዋል።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ ኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደኾነ ገልጸዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ለወባ ትንኝ መራባት ምክንያት መኾኑን ተናግረው የጸጥታ ችግር ባለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በታሰበው ልክ ሥራዎችን ለመሥራት እንዳልተቻለ ገልጸዋል። ዶክተር መሳይ የችግሩን አሳሳቢነት ሁሉም እንዲረዳው አሳስበው የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የበሽታ አስተላላፊ ትንኞች ላይ የዘረ መል ልየታ ቅኝት እንደሚሠራም መናገራቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ሰላኢ እና የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ፕሮግራም ዶክተር ፒተር የኢትዮጵያ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑ የሚበረታታ መኾኑን ገልጸው የወባ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሚደረጉ ሥራዎች ድጋፍ እና ክትትላቸው እንደሚቀጥል አሳውቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዒዱን በሰላም፣ በፍቅር፣ በመተባበር እና በመተሳሰብ እንድናሳልፈው አደራዬን አስተላልፋለሁ” ሼህ ጀውሃር ሙሐመድ
Next article“ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓልን ሲያከብር በአብሮነት እና በመረዳዳት መንፈስ ሊኾን ይገባል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ