
ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓልን ምክንያት በማድረግ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በመግለጫውም በዓሉን በፍቅር እና በሰላም ማክበር እንደሚገባ መልዕክት አሰተላልፏል፡፡
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ጀውሃር ሙሐመድ በመልዕክታቸው በሀገር እና በውጭ ለሚገኙ ሙስሊሞች ለ1ሺህ 445ኛው ዓመተ ሂጅራ ዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
“ዒዱን በሰላም፣ በፍቅር፣ በመተባበር፣ በመተሳሰብ እንድናሳልፈው አደራዬን አስተላልፋለሁ” ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሼህ አብድራህማን ሡልጣን የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል በክልሉ አንጻራዊ ሰላም በሰፈነበት ወቅት የሚከበር መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ሙስሊሙ ሲጠብቀው የነበረው ጠንካራ ሕዝባዊ የመጅሊስ ግንባታ በሁሉም ዞኖች ተዋቅሮ ታሪካዊ አማናውን ለመወጣት እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በታችኛው መዋቅር የሚገኙ የመጅሊስ አባላት ለሰላም መረጋጋት እና ለፈጣን የልማት እድገት መሳካት ለአፍታ ሳይዘናጉ በአንድነት እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የዓረፋ በዓል ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው እስማኤልን መሥዋዕት ያቀረቡበት ነው ያሉት ሼህ አብድራህማን ነብዩ መሐመድም የዓረፋ ቀን የስንበት ሐጂ ላይ ታሪካዊ ንግግር ያደረጉበት ቀን ነው ብለዋል፡፡
“ሙዕሚኖች ወንድማማቾች ናቸው፣ ደማችሁ እና ክብራችሁ በእናንተ ላይ እርም ነው፤ አደራችሁን ተወጡ” የሚለውን ነብያዊ ምክር በማጤን የማንንም መብት ሳንጋፋ ዒዳችንን በጋራ እንድናሳለፍ ለማሳሰብ እንወዳለን ነው ያሉት፡፡ ሰዎች ኾይ ጌታችሁ አሏህ አንድ ነው፤ የመጣችሁት ከአባታችሁ አደም ነው፤ ከእናንተ በልጦ አሏህን የሚፈራ ነው ትልቅ የሚባለው እንዳሉት በመከባበር፣ በመተዛዘን፣ እርስ በእርስ በመተሳሰብ በዓሉን እንድናሳልፍ በአሏህ ስም እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
የዒድ አል አድሃ በዓል አንድነታችንን የምናሳይበት፣ በአንድነታችን ለጌታችን የምንተናነስበት፣ በአንድነታችን ክብራችንን የምናሳይበት ቀን ነው ያሉት ሼህ አብድረህማን የተቸገሩት እርዳታችንን እንዲጋሩን በማድረግ ማስታወስ ከእኛ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ከሌሎች የሃይማኖት ተከታዮች ጋር የተለመደው መተሳሰብ፣ መከባበር እና መተዛዘን እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡
የዒድ አል አድሃ በዓል በሰላም እንዲከበር ኀላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችን አመሥግነዋል፡፡
ዒድ አል አድሃ በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተዛዘን፣ የመከባበር፣ የአንድነት እና የአሏህ እዝነት የሚወርድበት እንዲኾንም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሰላም የሁሉም መሠረት ነው፣ ኢስላም የሰላም ምንጭ ነው፤ ሀገራችንን አሏህ ሰላም ያድርግልን ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ሙሐመድ አንዋር በዓሉ የመተዛዘን፣ ችግረኞችን የምናስታውስበት፣ ደሃዎችን የምንጠይቅበት፣ አቅመ ደካሞችን የት አሉ ብለን የምናይበት፣ ደሃዎችን እኩል አድርገን የምናስተናግድበት፣ አይዟችሁ የምንልበት ነው ብለዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ስለ ሀገራችን ሰላም አሏህን የምንጠይቅበት፣ አንድነታችንን የምንሰብክበት፣ የሀገራችንን ውህደት እና የወደፊቱን ትብብር የምናጠናክርበት እንዲኾን አደራ እላለሁ ነው ያሉት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!